የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ እልቂት እያስከተለ፣ የዓለም አገሮችን በብዙ መልኩ እየፈተነ ይገኛል፡፡ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ተላላፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥርጭቱን ለመቀነስ የሚወሰዱ የእንቅስቃሴዎች ገደዶች አሉ፡፡ ድንበር ተሸጋሪ እንቅስቃሴዎችን እንዲቆሙ ማድረግ፣ የንግድ ተቋማት መዘጋት፣ የትራንስፖረት ገደብ መጣል የመሳሰሉት እርምጃዎች፣ መደበኛ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ አንቅፋት ስለሚፈጥሩ፣ ወረርሽኙ ከጤና ጉዳት ባለፈ ፈርጀ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንዲከሰቱ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሰዎች እንደ ልብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው በሙሉ አቅማቸው ማምረት፣ መገበያየት፣ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ በእጅጉ እየገደበ ያለው ወረርሽኙ፣ በኢኮኖሚ ላይ ከሚያደርሰው ጫና ባለፈ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን የማምረትና የማጓጓዝ ሂደቶችን በማደናቀፍ፣ የምግብ እጥረት አንዲከሰት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በተለያዩ አገሮችን ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡
በኢትዮጵያም ቢሆን የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ ከመጣ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ስለማይቀር በርካታ ዜጎች የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በተለይ በከተሞች መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ ተሰማርተው የጉልበት ሥራ ና ሌሎች መሰል የንግድ ሥራ ዎችን በመሥራ ት ላይ የሚገኙ፣ ኑሮኣቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ፣ በልመና በሚገኝ ድጋፍ ህይወታቸውን የሚገፉ አና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ ድጋፍ ካልተደረገላቸው ችግሩን ሊቋቋሙት እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በተከሰተበት በመጀመሪያዎቹ ቀናት በየገበያ ማዕከላት፣የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች የተስተዋለው የሸመታ ርብርብን ተከትሎ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሬ ታይቶ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምርቶችን በመደበቅ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት እንዲፈጠር በማድረጋቸው፣ በከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ ተፈጦሮ የነበረው ስጋት ይታወሳል፡፡ መንግሰት እህል በሚያከማቹና የዋጋ ንረት በፈጠሩ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ላይ እርምጃ በመውሰዱ ችግሩ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳይቶ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ያለው ሥርጭት አነስተኛ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር አሳይቷል፡፡ ምንም እንኳን ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በግልጽ ለመተንበይ ቢከብድም፣ ዓለም አቀፍ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ቫይረሱ በአፍሪካ ረዘም ላለ ጊዜ የመቆየት እድል እንዳለው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ይህ ረዘም የለ ወረርሽኝ ወቅት ሀገራቱን በተለያየ መልኩ ሊፈትን እንደሚችልም እየተነገረ ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ አሁን ባለንበት ሰዓትም ቢሆን በዓለም ላይ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ እያደረገ እንደሚገኝና ችግሩን ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ፣ ወረርሽኑን ለማስቆምና እንዳያገረሽ ለመከላከል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለምአቀፍ ድርጅቶች በሚያዚያ ወር አጋማሽ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡መንግስታት ቫይረሱን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ምግብ የምምረትና የማጓጓዝ ሂደቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መከወን እንዳለባቸውም ተገልጧል፡፡
የወረርሽኙ ሥርጭት በከፋባቸው አገሮችን የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ተብሎ የሚጣሉ እገዳዎች፣ የምግብ ነክ ዕቃዎችን የማጓጓዝ ሂደቶች ላይ እንቅፋት በመፍጠር፣ በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ጉዳት በማድረስ የምግብ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ለግብርና ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንደልብ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ፣ የምግብ ሰብሎችን በማምረት ሂደት ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ ለወትሮው በከፋ ድህነት ላይ የሚገኙ አገሮችን በምግብ እጥረት በእጅጉ ሊጎዱ እንደሚችሉም እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡
መሳይ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ኮሌጅ የልማት ፣ የምግብ ዋስትናና የአካባቢ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ላይ የሚኖረውን ጉዳት በተመለከተ ለሪፖርተር መጽሔት እንደገለጹት፣ ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ባሉ ድሀ አገሮችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ተደራራቢ ነው፡፡ በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ ከሄደ በሚዲርሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎች ምክኒያት ከሥራ ቸው የሚፈናቀሉ፣ ገቢያቸው የሚያሽቆልቆል፣ ተንቀሳቅሰው መሥራ ት ማይችሉ ወዘተ ዜጎች ለከፋ የምግብ እጥረት ችግር መዳረጋቸው አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም በከፋ የምግብ እጥረት ላይ የሚገኙና እርዳታ የሚሹ በርካታ ዜጎች ባሉባት ሀገር ችግሩን ተደራራቢ ያደርገዋል፡፡
የቫይረሱ ሥርጭት ወደ ገጠር እየተስፋፋ ከሄደ በግብርና ሥራ ላይ በተሰማራው የሰው ኃይል ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ባለሙያው አክለዋል፡፡ ይህም ምርት የማምረት፣ የመሰብሰብ፣ ከገበያ የማቅረብ ሒደትን በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ ይኸ ደግሞ የምግብ እጥረት አንዲያጋጥም ምክኒያት እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከገጠር ወደ ከተማ ይደረግ የነበረው የእርሻ ምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት መዳከም፣ በከተሞች የምግብ እጥረት አንዲከሰት ሊያደርግ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን የሚገልፁት መሳይ (ዶ/ር) ይህም ብቻ ሳይሆን የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ ተብሎ በትራንስፖርት ስርዓቱ ላይ በሚወሰዱ ገደቦች ሳቢያ፣ በበርካታ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ፡፡ የምግብ እጥረት ኮሮና ቫይረስ ካለፈ በኋላም ቢሆን ከፍተኛ ጉዳት ሊያዲርስ የሚችልበት እድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ግምት እነዳለም አክለዋል፡፡ በተለይ የከፋ ድህነት ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ለአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑትን በመለየትና በመደገፍ የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ለሪፖርትር መጽሔት ገልጸዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተነገረበት ዕለት አንስቶ መንግስት ወረርሽኑን ለመቆጣጠር ይረዳኛል ያላቸውን በርካታ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል፡፡ወረርሽኙን ተከትሎ የምግብ እጥረት ችግር አንዳያጋጥም በማሰበና የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ ከመጣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሆን የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በሀገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ዎች እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ዜጎች እርዳታ የሚሆን ምግብ ለማከማቸት በአዲስ አበባ ከተማ ከ1200 በላይ የምግብ ባንኮች በከተማ አስተዳደሩ የተዘጋጁ መሆኑ ታወቋል፡፡
ሀብትን ከባለፀጋው እየሰበበሰቡ ለድሆች ማካፈል የሚያስችል ሥርዓት ከዚህ ቀደም እንደሀገር ባለማዘጋጀታችን ምክኒያት በቀላሉ ተረዳድተን ማለፍ ለምንችላቸው ችግሮች የውጭ ዕርዳታ ስንጠብቅ መኞራችን አሳዛኝ መሆኑን የሚናገሩት መሳይ (ዶ/ር)፣ እንዲህ ያለው የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ በሰለጠኑት አገራት በርካታ ችግሮችን ሲፈቱበት ማየት የተለመደ መሆኑን ጠቁመው፣ “ያለንን ሀብት በአግባቡ ተካፍለን ይህንን ችግር መወጣት የምንችልበት መንገድ ስለሆነ፣ በአግባቡ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ለወደፊቱ ደግሞ የምግብ ባንኮቹ በአገር ደረጃ ተቋማዊ ቅርፅ ይዘው በአዋጅ መዋቀር ቢችሉ፣ ችግሮችን ለማለፍ የሚያግዙ ትልቅ አቅም ይሆናሉ” በለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ያሉ የአደጋ ጊዜያት ለሀብት መባከንና ለሙስና ስለሚመቹ፣ የሚሰበሰበው ሀብት ለታለመለት አላማ ብቻ ስለመዋሉ ማረጋገጥና ከሙስና አደጋ መጠበቅ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ አንደ ሀገር የሀብት አጠቃቀማችን እራሱ አባካኝነት ተሞላበት እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያው፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ሀብት የማባከን ልምዶች ቢስተካከሉ እንደ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቸጋሪ ወቅት ሲመጣ ከመደናገጥ ሊያድኑ እንደሚችሉ መሳይ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ ምክኒያቶች (አደጋዎች) ሳቢያ ዜጎቿን መመገብ የተቸገረችባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከዘመናዊ አሠራር ጋር የተጣላ የሚመስለው የሀገሪቱ ግብርና ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የሰው ሀይል ቢያሰማራም፣ ለአጠቃላይ የምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ማበርከት የቻለው 42 በመቶውን ብቻ መሆኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ የግብርናው ምርታማነት ከእለት ጉርስ ባለፈ የመጠባበቂያ የእህል ማከማቸት የሚያስችል አቅም እንኳን የሌለው በመሆኑ፣አንደ ሀገር እንዲህ ያሉ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በርካታ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡
የምግብ ሰብሎችን የማምረት ሒደት በዋናነት በግብርናው ዘርፍ የሚከወን ተግባር ነው፡፡ ገበሬው የሚያመርታቸው የምግብ እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በቀጥታ ለምግብነት ከመዋላቸውም ባለፈ ለምግብ አምራች ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ በመሆን ስለሚያገለግሉ፣ ምግብ በማምረቱ ሒደት ውስጥ ግብርናው ያለው ሚና የማይተካ ነው፡፡ ጠንካራና ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት የዘረጉ አገሮችን እንዲህ ያሉ የአደጋ ወቅቶች ሲያጋጥሟቸው ሊፈጠር የሚችልን የምግብ እጥረት የጎላ ችግር ሳያደርስ ሲቋቋሙት ይታያሉ፡፡ እንደ አገር ግብርናችንን ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ ከምግብ ችግር የምንወጣበት ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ግብርናው በዘላቂነት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከፖለቲካ ሽፋን ያለፈ ተጨባጭ ሥራ መሥራት ካልተቻለ የምግብ ዋስትናችን ማረጋገጥ ቀላል እንደማይሆንና ዘላቂ መፍትሄዎችን የግድ እንደሚል መሳይ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
ሌላው ባለሙያ ደግሞ አዳነ ተስፋዬ (ዶ/ር) በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ የኮሮና ቫይረስ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና በተለያየ መልኩ ሊጎዳ እንደሚችል ስጋታቸውን ለሪፖርተር መፅሔት ገልፀዋል፡፡ ዜጎች አንደልብ መንቃሳቀስና መሥራት ባለመቻላቸው ምክንያት በከተሞች በተለይ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርው በቀን ገቢ ኑሯቸውን ይደጉሙ የነበሩ ዜጎች፣ ገቢያቸው በማሽቆልቆሉ የተነሳ ለምግብ እጥረት ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ያለውን የምግብ ፈላጊ ቁጥር እንዲጨምር እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአንበጣና በአንዳንድ አካባቢ እያጋጠመ ያለው የጎርፍ አደጋ፣ በርካታ እንስሳትንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡ ሊያደርግ ስለሚችል ችግሩን የባሰ እንደሚያከብደው በማከል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
እ.ኤ.አ.በ2020 የሰብዓዊ ልማት ዕቅድ ላይ በተቀመጠው ግምት መሰረት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ስምንት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህ ቁጥር በአገሪቱ በተከሰተው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችንም ያጠቃልላል፡፡
ምን ይደረግ?
አሁን ካለንበት ሁኔታ ለግብርና የተሰጠው ትኩረት ከሚገባው በታች እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራዎችን ለማናወን ከፍተኛ የቀን ሠራተኞች እጥረት እያጋጠማቸው እንደሚገኝና የግብርና ግብዓቶች በሚፈለገው መጠን እየተሠራጩ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ የግብርና ሥራው እንደ አገር እጅግ በተቀናጀ መልኩ ሊደገፍ የሚገባበት ወቅት ነው ይላሉ፡፡ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአንበጣና የጎርፍ አደጋ ሥጋቶችም ቢሆኑ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ ክትትል በማድረግ ጉዳታቸውን በመቀነስ በምግብ ዋስትና ላይ የሚያደርሱትን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት ትኩረቱን ወረርሽኙን በመከላከል ላይ ማድረጉ ባይከፋም፣ የምግብ ዋስትና ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎች ከበሽታው ያልተናነሰ ቀውስ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ፣ በተቀናጀ መልኩ ተገቢውን ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡
የምግብና የምግብ ነክ ምርቶችን ማጓጓዙ በቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት ሊከናወን ይገባል፡፡ የምግብ እሴት ሰንሰለቱን በሚገባ በማደራጀትና በመከታተል ረገድ አገሮች ሌላው በትኩረት ሊሠሩት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
በግብርናም ሆነ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኩል ምግብ የማምረት ሒደቱን ማሳለጥ፣ ስብጥሩን የተጠበቀና የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የምርትና የግብይት ሒደቱ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን በተከተለ መልኩ መከወን እንደሚገባውም ሳይዘነጋ መሆን አለበት፡፡