አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ተጠቂዎች ቁጥር ከመቶ በላይ መድረሱ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል፡፡
አብዛኛዎቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች ከአዲስ አበባና ከሶማሌ ክልል የተገኙ ቢሆንም ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልልም በመገኘታቸው ወረርሽኙ ወደ ክልሎችም እየተሠራጨ መሆኑን ያሳያል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በተለይ ሚያዝያ 29 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም. በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች (29) በቫይረሱ መያዛቸውን ለመግለጽ እስከሚያዳግታቸው ድረስ በድንጋጤ ውስጥ ሆነው በመገናኛ ብዙኃን የተመለከታቸው ነዋሪም ሥጋቱ ይበልጥ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ “ወረርሽኝ” ሊያስብለው ይችላል ወይም አይችልም የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ እንዳለ ሆኖ፣ ሰሞኑን ግን የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሌሎች አገሮች የመመርመር አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ባደረጉት የተፋጠነ የምርመራ ሒደት፣ በርካታ ዜጐቻቸው በቫይረሱ መያዛቸውን ከማወቃቸው አንፃር ኢትዮጵያ ያላት የመመርመር አቅም ከአምስት ሺሕ የማይበልጥ ቢሆንም፣ እየመረመረች ያለችው ግን ከሙሉ አቅም በታች ማለትም ከ2400 ባለመብለጡ ቫይረሱ ወረርሽኝ በሚያስብል ደረጃ እንዳልተከሰተ አድርጐ መናገር እንደማይቻል ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሰሞኑን በቫይረሱ ተጠቅተው የተገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከሌሎች ታማሚዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸውና የጉዞ ታሪክም የሌላቸው ከመሆናቸው አንፃር፣ ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ መሆኑን እየገለጹ የሚከራከሩ በርክተዋል፡፡ በቫይረሱ የተጠቁ ዜጐች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ አንፃር፣ በኢትዮጵያ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ከ28 ሚሊዮን እስከ 3ዐ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚጠቁ የተነገረው ትንበያ እውነት እንዳይሆን በርካቶች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎችም፣ ጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች ቀደም ብለው ሕዝቡን ይመክሩ እንደነበረው አሁንም ተመሳሳይ ምክራቸውን እያሰሙ ነው፡፡