በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ በታኅሣሥ ወር የተቀሰቀሰው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ባለፉት አራት ወራት ውስጥ እንደሰደድ እሳት ተስፋፍቶ ከ200 በላይ አገሮችን አዳርሷል፡፡ እስካሁን በዓለም ዙሪያ በቫይረሱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲጠቁ፣ ከ290,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ወረርሽኙ በቀላሉ የሚሰራጭና ክትባትም ሆነ መድኃኒቱ እስካሁን በወጉ ያልተገኘለት በመሆኑ፣ ቫይረሱ እያስከተለ ካለው የጤና ቀውስ ባሻገር፣ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በመግታት በዓለም ሁለንተናዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል። ቫይረሱ ከሚያደርሰው የጤና ቀውስ ባልተናነሰ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ዓለምን እየፈተናት ይገኛል፡፡ ጠንካራ መሠረት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ያደጉ አገሮችን ኢኮኖሚ ሳይቀር እያሽመደመደ የሚገኘው ይህ አስከፊ ወረርሽኝ፣ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ሁለት ወር ሞልቶታል፡፡ ምንም እንኳን እስካሁን የቫይረሱ ሥርጭት በአንጻራዊነት (ቫይረሱ በስፋት ጉዳት ካደረሰባቸው አገሮች አንጻር) አነስተኛ ቢሆንም ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ሲባል እየተወሰዱ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የመግታት፣ ስብሰባዎችንና ሁነቶችን የመሰረዝ፣ ትምህርት ቤቶችን የመዝጋት ወዘተ እርምጃዎችን ተከትሎ፣ የምርታማነት መቀነስ፣ ፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፣ የእሴት ሰንሰለት መዳከም በመፈጠሩ ምክንያት በርካታ የንግድ ሥራዎች ላይ መዳከም እያስከተለ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ እንደየዘርፉና አካባቢው ቢለያይም በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች በተለይ ደግሞ አነስተኛና መደበኛ ባልሆኑ የንግድ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን እየገፉ በሚገኙ ዜጎች ላይ ጫናው እየበረታ ጉዳቱም እየታየ ነው፡፡
አልማዝ አበራ በአዳማ ከተማ የጀበና ቡና በመሸጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ኑሮዋን እየገፋች እንደነበር ትናገራለች፡፡ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን ተከትሎ በንግድ ሥራዋ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባትም ትገልጻለች፡፡ አብዛኛው ሰው የጀበና ቡና የሚሸጥባቸው ሲኒዎች ብዙ ሰው በጋራ ስለሚጠቀምባቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ያደርጋል በሚል ሥጋት የዘወትር ደንበኞቿ ሳይቀሩ ቡና መጠጣት እንዳቆሙ የምትናገረው አልማዝ፣ በቀን እስከ 150 ሲኒ ቡና ትሸጥ አንደነበር ገልጻ አሁን ግን ገበያዋ እጅግ እንዳሽቆለቆለ ምንም ካለመሸጥ ላይ እንደደረሰች ለሪፖርተር መጽሔት ተናግራለች፡፡
“ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ እንደተለመደው በጠዋት እየተነሳሁ ወደ ሥራ ቦታ እሄዳለሁ፡፡ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብዬ ውዬ የምሸጠው ከአምስት ሲኒ ቡና አይበልጥም፤” በማለት የምትናገረው አልማዝ፣ የደንበኞቿን ሥጋት ተረድታ ሲኒዎቿን በፈላ ውሃ እያጠበች ማቅረብ ብትጀምርም፣ በዕለት ሽያጯ ላይ ግን ምንም መሻሻል እንዳላየች ትናገራለች፡፡
እንደ አልማዝ ሁሉ ሪፖርተር መጽሔት ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው በየመንደሩ ዕቃዎችን በመሸጥ፣ የሴቶች ፀጉር በመሥራት፣ ልብስ በማጠብ፣ ምግብና መጠጥ በመሸጥ፣ መጽሐፍ በማዞር፣ ጫት በመሸጥና በመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የንግድ መቀዛቀዝ እንዳጋጠማቸውና ኑሮአቸውን ለመግፋት አንደተቸገሩ ይገልጻሉ፡፡ ለወትሮውም በከፋ ድህነት ውስጥ እንደነበሩ የሚገልጹት አብዛኞቹ ነጋዴዎች የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ሁሉም ነገር በአንዴ ቅይርይር ማለቱ አስፈርቷቸዋል፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከጽዳትና ንጽህና መጠበቂያ፣ ከምግብ ግብዓቶችና ከመሳሰሉ ምርቶች በስተቀር የአብዛኞቹ ሸቀጣ ሸቀጦች ፈላጊዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በየቦታው የሰዎች እንቅስቃሴ መቀነሱን ተከትሎ የአንዳንድ ምርቶች የገበያ ፍላጎት በመቀነሱ፣ እንዲሁም የምርት አቅርቦት ችግር የንግድ ሥራው እንዲዳከም ምክንያት ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ወ/ሮ ዓለምነሽ ታደሰ በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንችስ አካባቢ አነስተኛ ኮንቴነር ተከራይተው ምግብና መጠጥ በመሸጥ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቀነስ ተብሎ በሚሠሩበት አካባቢ የነበሩ በርካታ የምግብ ቤቶች እንዲዘጉ በመወሰኑ፣ የንግድ ሥራቸውን በማቆም በቤት ለመቀመጥ እንደተገደዱ ለሪፖርተር መጽሔት ተናግረዋል፡፡
“ሥራ ካቆምን ሁለት ወር ሊሆነን ነው፡፡ ራሴን ጨምሮ ሁለት ልጆቼን የማስተዳድረው ከምግብ ቤቱ በማገኘው ገቢ ነበር፡፡ አሁን ላይ ምንም ዓይነት ገቢ የለኝም፤” በማለት ይናገራሉ፡፡ ሥራ ካቆሙበት ጊዜ ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ መክፈል እንደተቸገሩና ቤተሰባቸውን ለመመገብ የሌሎችን ዕርዳታና ብድር እየጠበቁ መሆኑን በቁጭት ይናገራሉ፡፡ “የምንሠራባቸው የንግድ ቤቶች በመዘጋታቸው፣ ከነጋዴዎች በተጨማሪ በምግብ ቤቶቹ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች ከሥራ ውጭ በመሆናቸው ተቸግረዋል፤” በማለት ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳን ሥራቸውን ቢያጡም፣ ይሠሩበት የነበረው አካባቢ እጅግ የተጨናነቀ ከመሆኑ የተነሳ፣ በሽታን ከመከላከል አንጻር የተወሰደው ዕርምጃ ትክክል መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡
አሸብር አማረ፣ በደሴ ከተማ ጅብሩክ ተብሎ በሚጠራ የንግድ ቦታ በረንዳ ላይ በልብስ ስፌትና ተኩስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ራሱንና ቤተሰቡን ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡ የኮሮና ቫይረስ መግባቱን ተከትሎ በቀናት ጊዜ ውስጥ በሥራው ላይ ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ እንዳጋጠመውም ይናገራል፡፡ የቫይረሱ መከሰት ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ በከተማዋ የሰዎች እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት የቀን ገቢያቸው በእጅጉ በመቀነሱ ችግር ላይ መውደቁን ለሪፖርተር መጽሔት ተናግሯል፡፡
”እኔ በምሠራበት አካባቢ በልብስ ስፌትና ሌሎች ተመሳሳይ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራን በርካታ ግለሰቦች በቀን ገቢ የምንተዳደርና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለን በመሆናችን፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተፈጠረው የንግድ መቀዛቀዝ እያደረሰብን ያለውን ችግር ለመቋቋም ተቸግረናል፤” ሲል አሸብር ይገልጻል፡፡ ከሥራቸው ባህሪ አንጻር በቂ የሚባል ተቀማጭ ገንዘብ ስለሌላቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር እየተቸገሩ መሆኑንም አንስቷል፡፡ ይባስ ብሎ በዚህ ወቅት “መንግሥት ድጋፍ ያደርግልናል ብለን ስንጠብቅ የቦታ ኪራይና የአገልግሎት ክፍያ እንድንከፍል በከተማው አስተዳደር በኩል መጠየቃችን አስገርሞናል፤” በማለት ቅሬታውን ይገልጻል፡፡ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ እስከሚያልፍ በረዥም ጊዜ ክፍያ የሚመለስ የንግድ ሥራ መደጎሚያ ብድር እንዲሰጠን ቢደረግ እያልን በምንጠይቅበት ሰዓት ክፍያዎችን መጠየቃችን ችግራችንን አክብዶታል፤” በማለት የሚናገረው አሸብር፣ እንዲህ ያሉ የአገልግሎት ክፍያዎችና ኪራዮችን የምንከፍልበት ጊዜ ቢራዘምልን ጥሩ ነው ሲል ይጠይቃል፡፡
እስከ ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች 261 ሲሆኑ፣ 106 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል፡፡ አምስት ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ቫይረሱ በአገር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ በሚል በፌደራልና በክልል መንግሥታት የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ በማሰብ ባንኮች በኮቪድ 19 ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ በብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች እንዲሰጥ መወሰኑ ይገኝበታል፡፡
አብዛኞቹ በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦች የሚያንቀሳቅሱት ካፒታል አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ የሚያገኙትም ትርፍ ዝቅተኛ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ይህም ገቢ ከዕለት ጉርስ የሚያልፍ ባለመሆኑ እነዚህ ዜጎች በዚህ ወቅት የሚፈጠረውን የገቢ መቀነስ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ከባድ ነው፡፡ በተለይ የንግድ ቦታ ኪራይ፣ የሠራተኞች ደሞዝና ሌሎች ተደራራቢ ወጭዎች ያለባቸው ከሆነ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛዎቹ በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በመደበኛው የንግድ ሥርዓት ውስጥ የመካተት ዕድላቸው አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመንግሥትና በሌሎች አካላት የሚደረጉ ድጎማዎችንም ሆነ ድጋፎችን የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡
ሪፖርተር መጽሔት ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ መንግሥት ኮሮና ቫይረስ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ተገቢ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግን ለትላልቅ የንግድ ዘርፎችና ኢንዱስትሪዎች የተሰጠውን ግምት ያህል በአነስተኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች በተለይም መደበኛ ባልሆኑ ንግዶች ላይ ተሰማርተው ሕይወታቸውን በመግፋት ላይ ለሚገኙ በቂ ትኩረት የተሰጣቸው እንደማይመስል በመግለጽ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በከተሞች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በየሰፈሩ የተለያዩ ንግዶችን በመሥራት እየተዳደሩ እንደሚገኙ እንደሚታወቅ የገለጹት ባለሙያው፣ እነዚህ ዜጎች ራሳቸውን ከማስተዳደራቸው ባለፈ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያላቸው ድርሻ ቀላል ስላልሆነ፣ መንግሥት ለነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ንግዳቸውን ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የሚከውኑበትን ዘዴ በማመቻቸት ገበያ የሚያገኙበትን መንገድ መከተል ቢችል መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ፡፡
በተለይ አብዛኞቹ በአነስተኛ ንግድ ላይ የሚገኙ ዜጎች ሴቶችና ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው፣ በንግዳቸው ላይ የሚደርሰው ጫና ዘርፈ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ባለሙያው አክለውም መንግሥት ለነዚህ ዜጎች መጠነኛ ብድር እንዲያገኙ ሁኔታውን በማመቻቸት፣ የድጋፍና የክትትል ሥራ በመሥራት፣ የንግድ ሥራቸውን ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያግዙ ተግባራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በማመቻቸት ሊታደጋቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡