ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ እኔ ኮቪድ-19 ውዲቷን አገራችሁን ልጎበኝ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ የየዕለት ኑሯችሁን በጥልቀት እንድታዘብ ከፍተኛ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ዋነኛ የመወያያ ርዕሰ ጉዳያችሁ በመሆኔ ስለእኔም ሆነ ስለእናንተ ብዙ እንዳውቅ ረድታችሁኛል፡፡ በቆየሁባቸው ጊዜያት ስላለፈ ታሪካችሁ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎቻችሁ ብዙ ሰምቻለሁ፡፡ ብዙም አይቻለሁ፡፡ የእኔንም የእናንተንም መጨረሻ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንብኝ ይችን ደብዳቤ አስቀድሜ ልጽፍላችሁ ወደድኩ፡፡ የምር ግን ንትርካችሁን ተዋችሁት?
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች እውነቱን ለመናገር ዓለም በእኔ ጉዳይ ሲጨነቅ እናንተ የእኔ ጉዳይ ያሳስባችኋል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ያየሁት፣ ያደመጥኩትና ያነበብኩት ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ከአሁን አሁን ያለፉ ነገሥታትና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎቻችሁ ለኮቪድ-19 ወረርሺኝ መከሰት ተጠያቂ መሆን አለመሆናቸውን አንስታችሁ ትጋደላላችሁ ብዬ ብጠብቅ ይህንን ማድረጉ ትዝም አላላችሁ፡፡ እንደው ከእኔ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የዳግማዊ አፄ ምኒልክና የአፄ ዮሐንስ 4ኛ እጅ የለበትም ብላችሁ ነው? ቆይ ግን ከድሮ ታሪካችሁ እና ሥርዓተ መንግሥቶቻችሁ ጋር ሳታያይዙኝ ያለፋችሁኝ አስባችሁበት ነው ወይስ አድፍጣችሁ ነው? ቆይ እኔ ከማን አንሼ ነው “ብሔሩ ምንድን ነው? የማንስ ደጋፊ ነው?” ብላችሁ ጎራ ለይታችሁ ያልተነታረካችሁብኝ? አስባችሁበት ነው ወይስ አድፍጣችሁ ነው? አብዛኛውን ንትርካችሁን ረስታችሁ ትኩረታችሁ በሙሉ እኔ ላይ ሆነ! አስባችሁበት ነው ወይስ አድፍጣችሁ ነው? መምከር ሌላ መተገብር ሌላ፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን አብዛኛው የዓለም ክፍል ነዋሪ ወቅታዊ ምርጫ በሕይወት በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆኖ ሳለ የእናንተ ምርጫ በሽግግር መንግሥት እና በአገር አቀፍ ምርጫ መካከል ሆኗል፡፡ ተገቢ ባይሆንም የእናንተኑ ቃል ከታላቅ ይቅርታ ጋር ልጠቀምና “እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም” ትላላችሁና ከሰሞኑ ንትርካችሁ አገርሽቷል፡፡ ከሞላ ጎደል ግን አሁንም ስለእኔ መጨነቃችሁ መወያየታችሁ እና ማተኮራችሁ አልቀረም፡፡ እስዮ ነው መቼም!!! እንደሕዝብ ያለፈውን ተወት አድርጋችሁ ዛሬና ነገ ላይ ስታተኩሩ የመጀመሪያችሁ ጊዜ ይመስለኛልና ይልመድባችሁ፡፡
ወዲህ ወዲያ ስል ብዙዎቹን የአደባባይ፣ የጓዳና የብዙኃን መገናኛ ውይይቶቻችሁን ለማጤን ዕድሉን አግኝቻለሁና ብዙ ታዘብኩ፡፡በጣም የገረመኝ ግን ብዙዎቻችሁ እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቅንጣት ቫይረስ ሳልሆነ በዓይን የምታይና የምዳሰስ ሙክት መስያችኋላሁ፡፡ እናም ጥንቃቄያችሁ ሙክቱ እንዳይረግጣችሁ እንጂ ቅንጣቱ ቫይረስ ወደሰውነታችሁ እንዳይገባ የሚደረግ አይደለም፡፡ ደሞ ጥንቃቄውም ሆኖ መገኘት ቀርቶ መስሎ መገኘት ይበዛበታል፡፡ ትዝብቴን በየአንጓው ላካፍላችሁ፡-
ምልከታ አንድ፡-
ባለፈው ሰሞን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰዓት በኋላ ባስተላለፈው ቀዳሚ ዜናው አዲስ አበባ ውስጥ አንድ በጎ አድራጊው እኔን ለመዋጋት መንግሥታችሁ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ለአካባቢያቸው ነዋሪዎች ዘይትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን በአርአያነት ጠቅሶ ነጋሪት ጎሰመላቸው፡፡ በቲቪው መስኮትም ባለሃብቱ መኖሪያ ቤት በረንዳ ላይ ተደርድረው ከባለሃብቱ እጅ የሚሰጣቸውን ጥቂት መቶ ብሮች፣ በእጃቸው የያዙትን ዘይት እና እግራቸው ሥር ያለውን ጥቂት ቋጠሮ ማዳበሪያና የባለሃብቱን ደማቅ ፈገግታ ደጋግሞ ሲያሳይ አየሁኝ፡፡ ባለሃብቱም ከመኖሪያቸው በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያው ቅጽር ግቢ ውስጥ ተገኝተው ስለበጎነታቸው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኅብረተሰቡ ሊያደርግ የሚገባውን ጥንቃቄ ተነተኑ፡፡ ከተናገሩት መካከል የቫይረስ ደረቴ እስኪሰነጠቅ እጅግ በጣም ያሳቀኝን ላስታውሳችሁ፡፡ ጋዜጠኛውን እያመለከቱ “ … ከአካልህ የምርቀው ስለማስብልህ ነው! የማላቅፍህ ስለምወድህ ነው! …”አሉ፡፡ በጎ አድራጊው ምክራቸውን ከመስጠታቸው በፊትም ሆነ እየሠጡ ባለበት ወቅት ባለሃብቱ በመኖሪያ ቤታቸው ያደረጉት በጎ አድራጎት ሲዘገብ ዜና ትንታኔው በጋዜጠኛው ድምፅ ሲነበብና ዘገባው ሲሄድ በሚታየው ምስል እኚህ በጎ አድራጊ እያንዳንዳቸውን ክቡር የኢትዮጵያ ልጆች እጅግ በጣም እየተጠጉ ዘይትና ገንዘብ ሲሰጡና በስተመጨረሻም ከእያንዳንዳቸው ክቡር የኢትዮጵያ ልጆች ጋር እየተቃቀፉ ፎቶ ሲነሱና ዜናው የተሠራበትን ቪዲዮ ሲቀረጹ ይታያል፡፡ዘገባውን እንዳየሁት የቴሌቪዥን ጣቢያው ተመልካች እንጂ ኤዲተርም ሆነ አዘጋጅ እንደሌለው አረጋገጥኩ፡፡ እናስ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቫይረስ ነኝ ወይስ ሙክት በግ የማክል በሽታ አምጪ ተህዋስ?
ምልከታ ሁለት፡-
ደግሞ ሕዝብ በእኔ ላይ እንዲዘምት ለማነሳሳት የተዘጋጁ ናቸው የተባሉ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በብዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላያ እየተጋበዙ ይገኛሉ፡፡ ሐሳባችሁ ባልከፋ ግን ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ተመልካች እንጂ ኤዲተርም ሆነ አዘጋጅ የሌላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችሁ ስንት ናቸው? አንዱ የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ የኪነ ጥበብ ቡድን የላከልን ነው ብሎ አንድ “ዘፈን” ጋበዘ፡፡ ከዘፈኑ በፊት አዘጋጆቹ ቃለ መጠይቅ ሰጡ፡፡ “ዘፈኑን” ያዘጋጀነው ኅብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ … ለማስተማር … ነው“ ብለው ራሳቸውን መከሩ፡፡ ከዛ ጋዜጠኛው “ዘፈኑን” ጋበዘ፡፡ በቴሌቪዥኑ የተለቀቀው ዘፈን ግን እኔ ኮቪድ 19 ከመከሰቴ በፊት የተቀረጸ እንጂ አሁን የተሠራ አይመስልም፡፡ ዘፈኑን ለማጀብ የሚታዩት ደናሾች እርስ በእርሳቸው እንደችቦ ተጠጋግተው ቁና ቁና እየተነፈሱ በአካላዊ እንቅስቃሴ እንዴት ማስነጠስ እንዳለብን፣ እንዴት መታጠብ እንዳለብን … ያሳዩናል፡፡ እርስ በእርሳቸው እኮ እየተሸሹ ነው የሚደንሱት፡፡ ጋዜጠኛው ተመልሶ ራሳችንን ከኮቪድ 19 ለመጠበቅ ከዘፈኑ ጥሩ ትምህርት እንዳገኘን እምነቱ እንደሆነ ነግሯችሁ ሄደ፡፡ እናስ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቫይረስ ነኝ ወይስ ሙክት በግ የማክል በሽታ አምጪ ተህዋስ?
ምልከታ ሦስት፡-
በሌላም የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተለያዩ ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ባሉበት ውይይት ቀረበላችሁ፡፡ ውይይቱ ያው እንደፈረደብኝ በእኔ ላይ እንድትዘምቱ የሚያስተምር ነው። በውይይቱ ላይ ብዙ ነገሮች ተነስተው ውይይት ተደረገባቸው፡፡ ባለሙያዎቹም አካላዊ ርቀትን እንድትጠብቁ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማይተገብሩ ሰዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ወዘተ ገለጹ፡፡ ውይይቱ ሲያልቅ አዘጋጆቹ አመስግነው ተሰናበቱ፡፡ በውይይቱ መጠናቀቅ ላይ በሚታየው ምስል ግን ተወያዮቹ አንድ ቦታ ከጋዜጠኛው ጋር እጅብ ብለው ቆመው ሲወያዩና ሲሳሳቁ ይታያል፡፡ አሁንስ እኔም የገዛ ኅልዋቴን ተጠራጠርኩት! እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቫይረስ ነኝ ወይስ ሙክት በግ የማክል በሽታ አምጪ ተህዋስ?
ምልከታ አራት፡-
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በእኔ ጉዳይ ስትወያዩ እንዴት ፍዝዝ ብዬ እንደማያችሁ ብታውቁ ደስ ባለኝ፡፡ አሁን ባለፈው አንድ ሥጋ ቤት በር ላይ ጠረጴዛ ከበው የጦፈ ክርክር የሚያደርጉ ሰዎች ዘንድ እግሬ ጣለኝ፡፡ ከመካከላቸው እንዱ ብስጭት ብሎ ስልኩን አወጣ፡፡ ያለበቂና ታማኝ መረጃ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ እንደማይገባ በኃይለ ቃል ተናገረ፡፡
“… ይኸውላችሁ የኮሮና ቫይረስ ከያዘው ሰው የሚወጣው ትንፋሽ ይሄን ያህል ሜትር መጓዝ ይችላል የሚል አዲስ ጥናት ይፋ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ በሚዲያ ሲገለጽ ከነበረው ርቀት በላይ በደንብ መራራቅ ግድ ነው! …” እያለ መረጃ ነው የሚለውን አሳያቸው፡፡ በክርክራቸው መሃል ሌላ ጓደኛቸው መጣ፡፡ ወንበር ስቦ በአንድ ጠረጴዛ ላይ 8ኛ ሰው ሆኖ ተቀመጠ፡፡ ስለ አካላዊ ርቀት ክርክራቸውን ቀጠሉ፡፡ በነገራችሁ ላይ ከእነኚህ ሰዎች አንዱ በአንድ ቴሌቪዥን መስኮት በየዕለቱ በሚተላለፍ መልዕክት ላይ “ከቤት አትውጡ … በቤታችሁ ቆዩ” እያለ የሚያስተምራችሁ አርቲስት ነው፡፡ እሱን የሚመስሉ እልፍ እንደሆኑ እናንተም እኔም እናውቀዋለን፡፡ ግን እመኑኝ እኔ በዓይን የማልታይ ቫይረስ እንጂ ሙክት በግ የማክል በሽታ አምጪ ተህዋስ አይደለሁም፡፡
እጅ መታጠብ ትናንትና ዛሬ
የእጅ መታጠብ ልምዳችሁ የሚመስጥ እንደነበረ ከእኔ በፊት የሚያውቋችሁ ወዳጆቼ ነግረውኛል፡፡ በእንዲህ ቅጽበት የተቋማቱ ደጅ እጅ መታጠቢያ መገጠሙን ማየቴ ግን አስደምሞኛል፡፡ እጅ መታጠቢያዎቻችሁን ተደራሽ ማድረግ ትችሉ ዘንድ እኔ ሞት ይዤ እስከምመጣ መጠበቅ ነበረባችሁ? ሌላው ቀርቶ በአንዲት ቅንጣት የምሳ ሳህን የአምስት መቶ ብር ምሳ የሚሸጡ ሆቴሎቻችሁ ያቀርቡላችሁ የነበረው ፈሳሽ ሳሙና በውሃ ከመቅጠኑ የተነሳ ከደረቅ ሶፍት በተሻለ እጃሁን አያጸዳም ነበር፡፡ በትክክል ሳሙና እንዲያቀርቡላችሁ እንደውም የጤና ተቋሞቻችሁ ይቆጣጠሩ ዘንድ እናተም እንደተገልጋይ ተገቢው ሳሙና ይቀርብላችሁ ዘንድ ለመጠየቅ እንድትችሉ እኔ ሞት ይዤ መምጣት ነበረብኝ?
በመዲናችሁ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሱፐር ማርኬት በር ላይ የተቀመጠውን ሳሙናና ማስታጠቢያ ስንቶቻችሁ አይታችሁት ይሆን፡፡ ሳሙናን ጨምሮ ውድ የሆኑ የንጽህና ዕቃዎችን የሚሸጠው ይህ ተቋም ለደንበኞቹ ደኅንነት ደጅ ላይ ያስቀመጠው ሳሙና በውሃ ከመቅጠኑ የተነሳ በውሃ ውስጥ የጠለለው ቆሻሻ ይታይ ነበር፡፡ በድርጅቱ የተናቀው የድርጅቱ ተገልጋይ የሚታጠብበት ውኃ የሚጠራቀመው በሰፊ ልብስ ማጠቢያ ሳፋ ላይ ነው፡፡ ይሄንን ውኃ ለመያዝ በማይመች መልኩ ወደ አስፋት እያመላለሱ የሚደፉት የድርጅቱ ጥበቃዎች ናቸው፡፡ በሥራ መዘርዝራቸው ላይ ውኃ መድፋት ይኖር ይሆን? ይህንን ውኃ የድርጅቱ ባለቤቶችና አመራሮች ድፉት ቢባሉ ይነኩት ነበር?
ይህንን ድርጅት ጠቀስኩላችሁ እንጂ በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ ባንኮችን ጨምሮ ከኪራይ ብቻ የሚያገኙት ገቢ የአንድ ቀበሌ የውሃ ፍጆታን መከፈል የሚያስችላቸው ባለሃብቶች የ60 ብር ባሊ በራቸው ላይ አስቀምጠውላችኋል፡፡ የተጣራ የዓመት ገቢያቸው ከከተማ ወጥተው አንድ ሳምንት ለመዝናናት የማይፈቅድላቸው ትናንሽ ንግድ ቤቶች ግን ከንክኪ ነፃ የሆነ የሳሙና እና የውኃ አቅርቦት በደጃቸው ላይ አኑረው ይጠብቋችኋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃኖቻችሁ ግን አያስታውሷቸውም፡፡
ድፍረታችሁ የሚሰጠኝ ደስታ
የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ በራስ የመተማመን ልካችሁ ምን ያህል ነው? መቼም እኛን አይነካንም! ታላቆች ነን! የፈጣሪ ቀኝ እጅ ነን ያላችሁ የሰው ዘር ሁላ እንዴት እንደሆናችሁ እያያችሁ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የሰው ልጅ በራስ የመተማመን ጠገግ እንደ እኔ የፈተነ ያለ አይመስለኝም፡፡ ወራሪ ካልመጣባችሁ “እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሄ አቅም አለን … ማንም አይበግረንም!…” ስለማትሉ በሌሎች ትምክህት እንደተበሳጨሁት በእናንተ አልተበሳጨሁም፡፡ እንደው ከእኔ መከሰት ወዲህ ግን አዲስ ነገር እያየሁባችሁ ነው፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ይሄ አቅም አለን፣ ይህንን ማምረት ያኛውን መፍጠርና መፈብረክ እንችላለን ወዘተ እያላችሁ ነው፡፡ ከነፈተናችሁ ይህንን ስሜታችሁን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ትረቱኝ እንደሆን አብረን እናየዋለን፡፡ ትንሽ ግር ያለኝና ያሳዘናችሁኝ ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስለተሠሩ “የፈጠራ ሥራዎች” ስትዘግቡ የድፍረታችሁ መብዛት ሐፍረት እየሳጣችሁና የሙያ ሥነ ምግባራችሁን ታላቅ ጥያቄ ውስጥ እየከተተው መሆኑን እያስተዋልኩ ነው፡፡
በዙሪያችሁ ያሉ መገልገያዎቻችሁ ሁላ ከግለሰቦች የመነጩ የምርምር ውጤቶች እንደሆኑ ከእኔ በላይ እናንተ ታውቁታላችሁ፡፡ ለወትሮስ የሥልጣኔያችሁ መገለጫ የሆኑ ሥራዎችን ለመለወጥ ወስናችሁ ከተነሳችሁና ከተባበራችሁ ምን መሥራት እንደምትችሉ ጠንቅቀው ሲሰብኳችሁ ኖረዋልና ከልጅ እስከ አረጋውያን ድረስ አዲስ የምርምር ሥራ ለመሥራትና ዓለምን ለመለወጥ ምን ያህል አቅም እንዳላቸው ለእናንተ አይነገረም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የምርምር ሥራ በቂ ጊዜና የምርምር ሔደቶችን ማለፍ እንዳበት ከምርምር ሒደት በኋላም ምርቱ በደረጃና ተስማሚነት ተቋማት ይሁንታ ማግኘት እንዳበት በአገራችሁ ላሉ ጋዜጠኞች የሚነገር ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሄ ግን የተዘነጋ ይመስለኛል፡፡
በየዕለቱ በእገሌ እንዲህ የተባለ መሣሪያ ተሠራ፣ ተፈጠረ ወዘተ የሚሉ ዜናዎች በድፍረት እያስተላለፋችሁ ነው፡፡ ባለፈው በአንድ የቴክኒክ ትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤት ከመግባቱ በፊት በአንድ ዳስ ውስጥ በመግባትና የኬሚካል ርጭት በማድረግ ሰውነቱ ላይ ያለን የኮሮና ቫይረስ ሙሉ ለሙሉ ሊያጠፋ የሚችል መሣሪያ መፈብረኩን በዜና አሰማችሁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ለጽኑ ሕሙማን ሕክምና የሚውለውን ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ታላላቆቹ አምራቾች እንኳን በብዛት ለማምረት ምጥ የሆነባቸውን የመተንፈሻ መሣሪያ በኢትዮጵያ ተሠራ ብላችሁ እየተቀባበላችሁ ስትዘግቡ ከረማችሁ፡፡
ዘገባው አንድ ኢትዮጵያዊ 69 ኢንች ቴሌቪዥን ሠራ የሚል ቢሆን ኖሮ ምን አድርጋችሁ ልትዘግቡት ነበር? አንድ ቴሌቪዥን ያለውን መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚሰጥ መሆኑን እየከፈታችሁ እያሳያችሁን አትዘግቡትም ነበር? ቴሌቪዥኑ ተከፍቶ አታሳዩንም ነበር? መተንፈሻ ተሠራ ማለትስ ምን ማለት ነው? ተሠራ የተባለው መተንፈሻ በሰው አፍ ላይ ተገጥሞ ተሞክሯል? በጽኑ ሕመም ላይ ያለ ሰው ሊጠቀምበት ይችላል? መሞከር ወይም መፈተሸ ቀርቶ ተፈጠረ የተባለውን ማሽን አንድ ኢትዮጵያዊ ሐኪም በዓይኑ አይቶታል? የአገራችሁ የተስማምነት እና የደረጃ ተቋማትስ አይተውታል? ለመሆኑ ታላቁ አትሌታችሁ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ወደ ኦሊምፒክ ውድድር ሊሳተፍ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ጉዞ ሲጀምር “ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በኦሊምፒክ 10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸነፈ” ብላችሁ ነበር የምትዘግቡት?
ለመሆኑ “ፈጠራ”፣ “ግኝት”፣ “አስመስሎ መሠሥራት”፣ “የቴክኖሎጂ ሽግግር”፣ “የፈጠራ ሒደት”፣ “የምርምር ሥራ ተጀመረ” … ወዘተ በሚሉት ቃላትና ሐረጋት መካከል ያለውን ልዩነት ጋዜጠኞቻችሁና የዜና ክፍል መሪዎቻቸው ያውቋቸዋል፡፡ ወይስ ዜናውን የሚጽፉላችሁ የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ናቸው?
ኃላፊነት ከስምና ዝና ወይም ወረት በላይ ሲሆን
ብዙዎቻችሁ እንደምትሉት አገራችሁ የወላድ መካን አይደለችምና በዚህ ሁላ መሃል የምግባር ሰዎች የሆኑ ወገኖቻችሁ ጥቂት አይደሉም፡፡ ግለሰባዊም ሆነ ተቋማዊ ኃላፊነት ከዝናና ከክብር በላይ የሆነባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህንን አደረግን ብለው ነጋሪት ሳያስጎስሙ ሥራቸው ራሱ ያንጸባርቃል፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ በሚያደርጉት ጥንቃቄም ሆነ ባገኙት አጋጣሚ ራሳቸውንም ሆነ ወገኖቻቸውን የሚጠብቅና የሚጠቅም ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነሱን አንግሧቸው! አባዟቸው! ከእኔ ሊያስጥላችሁ የሚችለው የራሳችሁ፣ የእነሱና የመሰሎቻቸው ድርጊት ነው፡፡ ግለሰባዊ፣ የዜግነትና መንግሥታዊ ኃላፊነቶቻቸውን በታላቅ ሐቀኝነት የሚወጡቱ እነሱ፣ በእርግጥም የእናንተ ወዳጆች፣ በእርግጥም የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ናቸው፡፡ እነሱን አክብሯቸው!!! አንግሧቸው!!! አባዟቸው!!!
በመንግሥት የማታሳብቡበት ምክንያት መጣ
እኔን ከአገራችሁ ጠራርጋችሁ ለማስወጣት በእርግጥም የመንግሥት ኃላፊነት ትልቅ ነው፡፡ ክፋቱ ግን እንደ አገር ለመውደቁ፣ እንደቤተሰብ በድህነት ውስጥ ለመሆኑ፣ እንደ ማኅበረሰብ ለመፈረካከሱ፣ እንደ ግለሰብ ለመውደቁ ምክንያት የሆነውና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ብቻ ነው ብሎ ሲያሳብብ ለኖራችሁት ለእናንተ ለወሬም ለማመካኘትም የማልመቸው እኔ መጥቼላችኋለሁ፡፡
እጃችሁን ደጋግማችሁና በአግባቡ ላለመታጠባችሁ፣ አካላዊ ርቀታችሁን በአግባቡ ላለመጠበቃችሁ፣ ያለበቂ ምክንያትና ያለጥንቃቄ ከተማውን ስታካልሉ ለመዋላችሁ፣ በየመጠጥና ጫት ቤቱ ተፋፍጋችሁና በር ዘግታችሁ በመጠጥ ስትራጩና ጫት ስታኝኩ ውላችሁ ለማምሸታችሁ፣ የአፍ መሸፈኛችሁን እንደ ከረባት አንገታችሁ ሥራ ወትፋችሁ ለመዞራችሁ፣ መጽዳትና መታጠብ የሚችለውን የአፍ መሸፈኛችሁ ቆሻሻ ተከማችቶበት ከላያችሁ ላይ አልወልቅ ለማለቱ፣ በእግር ልትወጡት የምትችሉትን መንገድ በመኪና ካልሄድን ብላችሁ ታጭቃችሁ ለመሄዳችሁ፣ ሕፃናት ልጆቻችሁን ያለምክንያት በየንግድ ተቋሙና ሰው በየተሰበሰበት ሰብስባችሁ ያለጥንቃቄ ለመውጣታችሁ፣ የንግድ ተቋማት ለሚሰጧችሁ የጥንቃቄ ዕርምጃ ንቀታችሁን ለማሳየታችሁና ለጸብ ለመጋበዛችሁ፣ … እስቲ መንግሥትን ውቀሱት! እስቲ ያለፈ ታሪካችሁን ውቀሱ እርገሙ! እስቲ ወላጆቻችሁን ውቀሱ ተጠያቂም አድርጓቸው።
ዕድሜ ለእኔ ጣትን ወደራስ መሰብሰብ እንጂ ወደሌላ መቀሠር ከሞት የማያድንበት ጊዜ አሁን መጥቶላችኋል፡፡የየራሳችሁ ድርጊትና ኃላፊነት ወስዳችሁ የምታከናውኑት እያንዳንዱ የጥንቃቄ ዕርምጃ ራሳችሁንም፣ ሌላውን ወገናችሁንም፣ እናት አገራችሁ ኢትዮጵያንም፣ ጎረቤት አገሮቻችሁንም ሆነ ዓለምን ከእኔ ለመታደግ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ስለዚህ ኃላፊነት ውሰዱ! እያንዳንዳቸሁ ለውጥ ማምጣት ትችላችሁ፡፡ እናም በእኔ ልክ እኔን ለመመከት የሚያስችላችሁን ጥንቃቄ አድርጉ! እንዳልፈራችሁኝ ሳውቅ እበሳጫለሁ፡፡ “ፍጃቸው ፍጃቸው” ይለኛል። ሲከፋኝና ስቆዝም “ምናለ እኔ ኮቪድ 19 እንደሚፈረጥጥ በሬ ወይም እንደ ካፊያ ዝናብ እንኳን ቢያከብሩኝ?” እላለሁ፡፡
ብዙዎቻችሁ እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቅንጣት ቫይረስ ሳልሆን በዓይን የምታይና የምዳሰስ ሙክት መስያችኋለውና እኔ ኮቪድ 19 በዓይን የማልታይ ቅንጣት ቫይረስ መሆኔን አትርሱ፡፡ በልባችሁ አኑሩት፡፡ ጥንቃቄያችሁም በዓይን የማይታይና የማይዳሰስ ቫይረስን እንደሚዋጋ ሰው ይሁን፡፡ ቢያንስ ጭቃ እንዳይነካችሁ የምታደርጉትን ጥንቃቄ ያህል አድርጉ!!! በመሃላችሁ መኖሬን አትዘንጉ፡፡
ዛሬ ምልከታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሐሳብ ብቻ የምንሞግት፣ ካለፈው ይበልጥ በመጪው ላይ የምናተኩርና ምንጊዜም ለእናት አገር ኢትዮጵያችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች እንሁን!!! ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ!!! ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በትምህርት ዝግጅታቸው የሕግ ምሩቅ (LL.B, LL.M, MSW) ሲሆኑ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው። ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘትይችላል፡፡