የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ችግር ከሆነ ወራትን እያስቆጠረ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሳይንቲስቶች በደረሱበት የምርምር ደረጃም በትክክል የሚተላለፍባቸው መንገዶች በሙሉ ተለይተው አልታወቁም፡፡ ነገር ግን በሽታው በሰዎች መካከል በሚኖር ቀጥተኝ (መጨባበጥ፣መተቃቀፍ፣በማስነጠስ..) እና ቀጥተኛ ባልሆነ (አንድ ሰው የነካውን ግኡዝ ነገር ሌላ ሰው በመንካት …) አካላዊ ንክኪ እና የትንፋሽ ግንኙነት በቀላሉ የሚተላለፍ መሆኑ በትክክል ይታወቃል፡፡ ይህ ከሰዎች ባሕሪ ጋር በቀጥታ የተገናኘ የመተላለፊያ መንገዱ በሽታውን እጅግ አደገኛ እና አስፈሪ አድርጎታል፡፡ በሽታው ምንም ዓይነት ፈዋሽ መድሀኒት የሌለው መሆኑ እና ከሰው ወደሰው የሚተላለፍበትና የሚሰራጭበት ፍጥነት በድምር ሲታይ ብሔራዊ ሥጋት ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል፡፡ በበሽታው የፈጠረው ብሔራዊ ሥጋትም ተራ ሥጋት ሳይሆን ከፍተኛ እና ከባድ ሥጋት ነው፡፡
በሽታው ምንም ዓይነት ፈዋሽ መድሀኒት የሌለው ከመሆኑ አንፃር ያለው ብቸኛ መዳኛ መንገድ በበሽታው ላለመያዝ አስቀድሞ የሚደረግ የመከላከል ተግባራትን መፈፀም ብቻ ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ከበሽታው አስቀድሞ መከላከያ መንገዶች አድርገው በዋናነት የሚጠቅሷቸው ዘዴዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና ንፅህናን መጠበቅ ናቸው፡፡
አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚለው የመከላከያ ዘዴ ሰዎች በቤታቸው ተቀምጠው ራሳቸውን ከሌላው ኅብረተሰብ ከልለው እንዲቀመጡ ከማድረግ ጀምሮ በሥራ፣ በትራንስፖርትና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥም ቢያንስ የሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ርቀትን በማስጠበቅ እንዲንቀሳቀሱና አገልግሎት እንዲገኙ ማድረግን የግድ ይላል፡፡ ይህን በከተማ ብሎም በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ እና ተግባራዊነቱን መከታተል እና መቆጣጠር ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ በዚህ መሀከል የሚፈፀም ትንሽ ስህተት ተቆጥሮ የማያልቅ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ወይም አደጋ ላይ የሚጥል ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡
የኅብረተሰብን ጤና መጠበቅ እና ከተላላፊ በሽታዎች የመከላከል ተግባር የመንግሥት መደበኛ ስራ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 301/2006 አንቀጽ 5/2 መሠረት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ የመለየት እና በቂ ዝግጅት በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በተገቢው ሁኔታ የመከላከል ሥልጣን እና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 6 እና 7 መሠረት የጤና ሚኒስቴርም ወረርሽኝ እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን የመቀየስ እና የኅብረተሰቡን ጤና ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመከላከል እርምጃዎችን የመውሰድ እንዲሁም ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አፋጣኝ እና ውጤታማ መፍትሔ የመስጠት ሥልጣን እና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡
ከእነዚህ ድንጋጌዎች በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው እንደ ኮሮና (ኮቪድ-19) ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን በተመለከተ መንግሥት የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የሚከተለው ስትራቴጂ የኅብረተሰብን ጤና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ሥጋቶች የመከላከል ስልትን ማእከል ያደረገ ዘዴን ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ መንግሥት የኮሮና (ኮቪድ-19) በሽታን የሕክምና ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብን መሠረት ባደረገ ሁኔታ የመከላከል ስልትን ማዕከል ያደረጉ የመከላከል ተግባራትን በኅብረተሰቡ እንዲፈጸሙ የማስተማር፣ የማሳወቅ እና እንደ ሁኔታው የማስገደድ ተግባራትን ማከናወኑ መደበኛ የመንግሥት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ያሳያል፡፡
ነገር ግን የኮሮና (ኮቪድ-19) በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት እና የሚሰራጭበት ፍጥነት እጅግ ፈጣን (Exponential) በመሆኑና ይህን የአደጋ ሥጋት ለማስወገድ የሚከናወነው የመከላከል ተግባር የኅብረተሰቡን መደበኛ ኑሮ የሚያናጋ እና ብዙ ውዝግቦችን የሚያስነሳ ከመሆኑ አንጻር፣ እንዲሁም በሽታው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ፣ የመከላከሉ ተግባር በመደበኛ የመንግሥት ሥራ ሊከናወን የሚችል አይደለም፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 መግቢያ ላይ፣ ኮሮና (ኮቪድ-19) በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተሠራጨና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ወረርሽኝ በመሆኑና በመደበኛ የመንግሥት አሠራር ሥርዓት ሥርጭቱን መከላከልና መቆጣጠር የማይቻል ስለሆነ፣ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማውጣት አስፈላጊነት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1189/2012 መፅደቁን ተከትሎ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ማስፈፀምያ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 456/2012 መግቢያው ላይ የደንቡን መውጣት አስፈላጊነት ሲገል፣ ደንቡ የወጣው የመከላከል ሥራውን ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ የመብት እገዳዎችን እና ዕርምጃዎችን ለመወሰን መሆኑን ይገልጻል፡፡
የኮሮና (ኮቪድ-19) በሽታን የመከላከል ተግባራት በተለይ በሕክምና ባለሙያዎች ከሚሰጡት ምክረ ሐሳቦች አንጻር ሲታይ፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብና በእንቅስቃሴ ጊዜያትም ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት ከሚጠቀሟቸው አልባሳት በተጨማሪ አስገዳጅ የሆኑ የፊት መሸፈኛ ማድረግን እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅን አስገዳጅ የሚያደርጉ፣ እንዲሁም እነዚህን ጥንቃቄዎች በቀላሉ መፈፀም በማይቻልባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙ ማስገደድን እና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ የማያስችሉ አገልግሎት መስጫዎችን፣ አገልግሎት እንዳይሰጡ መዝጋትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህን ለመፈጸም ሲባል በሕገ መንግሥቱ ሕጋዊ ጥበቃ ከሚደረግላቸው መሠረታዊ መብቶች ውስጥ የሚገደቡ መብቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ብቻ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶች በሙሉ የሚታገዱ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የሚታገዱት መብቶች የትኞቹ እንደሆኑና በምን መጠን እንደሚታገዱ የሚወሰነው በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93/4 ሀ እና ለ መሠረት በግልጽ ተደንግጓል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ በማውጣት በመሠረታዊ መብቶች ላይ ገደብ ለማድረግ ያለው ሥልጣን ልቅ ወይም ያልተገደበ ሥልጣን አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ገደብ የሚደረግባቸው በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶች የትኞቹ እንደሆኑ እና ገደብ የሚደረግባቸውም በምን መጠን እንደሆነ በሚወስንበት ጊዜ፣ መመዘኛ አድርጎ ሊወስደው የሚገባው ዋናው ነጥብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ (የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን) ለማስወገድ አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት እና የገደቡ መጠንም በዚሁ እሳቤ ምን ያሕል እንደሆነ በመወሰን ነው፡፡እዚሕ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን የመብት ገደብ ሲያደርግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማስወገድ ከሚያስፈልገው የመብት ገደብ በላይ ገደብ ቢያደርግ፣ ይህን በምን መንገድ ማረም እና ማስተካከል ይቻላል የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ጥያቄ ከዚህ ጽሑፍ አላማ ውጭ ስለሆነ አንባቢ በራሱ መንገድ ምላሽ እንዲሰጠው በማድረግ አልፈነዋል፡፡
የኮሮና በሽታን የመከላከሉ ተግባር በዋናነት የሰዎች እንቅስቃሴን እና ግንኙነትን መገደብን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የኮሮና ቫይረስ (ወረርሽኝን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣው የማስፈጸምያ ደንብ ገደብ የሚያደርግባቸው መብቶች የበሽታውን ስርጭት ለማቆም ወይም ለመቀነስ በሚያስችል መጠን፣ የሰዎች እንቅስቃሴን እና ግንኙነትን መገደብን ማእከል ያደረገ እና የእነዚህ ገደቦችን ማስከበር እና ማስፈጸም የሚቻልበትን እንዲሁም ከገደቦቹ እና በበሽታው ከሚደርሱ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ የሚቻልባቸውን ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከት እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በዚህ መሠረት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በሽታን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 456/2012 የመብት ገደቦች መደረጉን እና የተገደቡት መብቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር ይገልጻል፡፡ ገደብ የተደረገባቸው መብቶችም የተከለከሉ ተግባራት በሚል ርእስ ስር በደንቡ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 27 ድረስ በተቀመጠ ዝርዝር ተገልጸዋል፡፡
ከነዚሕ ገደብ ከተደረገባቸው መብቶች ውስጥ የዚሕ ፅሁፍ አላማ የሆነው በማረምያቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እና ታራሚዎችን የሚመለከተው ክልከላ ነው፡፡
በማረሚያ ቤት ያሉ እስረኞች የተከሰሱ እና የታሰሩ ሰዎች በመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ላይ ስለተከሰሱ ሰዎች የተገለፁት መብቶች እና በአንቀጽ 21 በጥበቃ ስር ስላሉ እና በፍርድ ስለታሰሩ ሰዎች የተገለፁት መብቶች ይመለከቷቸዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 መሠረት አንድ ተከሳሽ ሲከሰስ በመደበኛ ፍርድ ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በግልፅ ችሎት ጉዳዩ የመስማት መብት፣ በሕግ በተገለፀ ሥርዓት ጉዳያቸው በዝግ ችሎት መታየት ያለበት ካልሆነ በስተቀር በግልፅ ችሎት የመዳኘት፣ የክሱን ኮፒ የማግኘትና የክሱን ዝርዝር የመረዳት፣ የቀረበበትን ምስክር የመጠየቅና የቀረበበትን ማስረጃ የማየት እንዲሁም የመከላከያ ማስረጃዎቹ እንዲቀርቡለትና እንዲሰሙለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡
ተከሳሹ መከራከሪያውንና መከላከያ ማስረጃውን እንዲያዘጋጅና በዚህ ሒደት ውስጥ ከጠበቃው የሙያ ድጋፍና የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ፣ በፍርድ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በተሰጠው ፍርድ ላይ ተፈፅሟል የሚለውን የሕግና የፍሬ ጉዳይ ስህተት በይግባኝ እንዲታረም የማድረግ መብት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ይግባኝ በወንጀል ጉዳዮች ሕገመንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው መብት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 መሠረት፣ አንድ ሰው በእስር ላይ ባለበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛው፣ ከቅርብ ቤተሰቡ፣ ከጓደኛው፣ ከሃይማኖት አባቱ፣ ከሐኪሙና ከሕግ አማካሪው ጋር የመገናኘት እንዲሁም እንዲጎበኘው ዕድል የማግኘት መብት አለው፡፡ እነዚህ መብቶች በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶች በመሆናቸው ገደብ ሊደረግባቸው የሚችለው በሕገ መንግሥቱ በተገለፀው ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተዘረጋው ብቸኛ ሥርዓት ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 456/2012 ላይ በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎችን በተመለከተ የተደረገውን ገደብ ስንመለከት በደንቡ በተራ ቁጥር 9 ላይ “ማንኛውንም ታራሚን ወይም ተጠርጣሪን በአካል በመገኘት በማረሚያቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ መጎብኘት ክልክል ነው፤” የሚለው ክልከላ ብቻ መደንገጉን እንረዳለን፡፡ በዚህ ደንብ መሠረት በማረሚያ ቤት ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ገደብ የተደረገባቸው ከቤተሰቦቻቸው፣ ከትዳር ጓደኞቻቸው፡ ከሃይማኖት አባቶቻቸው፣ እና ከሐኪሞቻቸው ጋር ለመገናኘት ባላቸው መብት ላይ ብቻ ነው፡፡ እስረኞች ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብታቸው አልተገደበም፡፡ ይልቁንም በደንቡ አንቀጽ 4/14 መሠረት የፖሊስና የማረሚያ ቤት ተቋማት ታሳሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ በማረሚያቤት በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በሕ መንግሰቱ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብቶቻቸው በሙሉ ገደብ አልተደረገባቸውም፡፡ በተለይ ጉዳያቸው በፍርድቤት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲታይላቸው ለማድረግ ያላቸው መብት በማናቸውም ሁኔታ አልተገደበም፡፡ ደንቡ እስረኞች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ለማድረግ ባላቸው መብት ላይ ገደብ ያላደረገ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እንደ ፍርድ ቤት ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞቻቸውም ሆኑ አገልግሎት ተቀባዮች አካላዊ ርቀቶቻቸውን እንዲጠብቁ በማድረግና ተጨማሪ ጥንቃቄ ተግባራትን በማከናወን፣ አገልግሎቱ እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነትን በመሥርያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ የሚጥል በመሆኑ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ማረሚያ ቤትና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቀናጅተው በመሥራት እስረኞቹ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ጉዳያቸው እንዲታይ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡
አሁን ባለው እውነታ ግን በማረሚያ ቤት ያሉ እስረኞች፣ ፍርድ ቤቶች በከፊል በመዘጋታቸው ምክንያት የፍርድ ሒደታቸው በመጀመርያ የክርክር ደረጃም ሆነ በይግባኝ ደረጃ ታግዶ ይገኛል፡፡
የችሎቶች በከፊል መዘጋት በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ክርክሮቻቸውን የማቅረብ፣ የቀረበባቸውን ምስክር የመስማት እና መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ፣ የመከላከያ ምስክር የማሰማት፣ ማስረጃ የማቅረብ፣ ፍርድ የማግኘት እና ይግባኛቸውን የማሰማት እና የመከራከር ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ያላቸው መብቶቻቸው መታገድን አስከትሏል፡፡ ፋይሎቻቸው እነሱም ሆኑ ጠበቆቻቸው በሌሉበት እንዲቀጠር እና ያለምንም የፍርድ ሒደት በእስር ላይ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህን ከእስረኞች አንጻር ስንመለከተው ሊመለስም ሆነ በማናቸውም ሁኔታ ሊካስ የማይችል ከባድ ጉዳትን ያስከተለ ተግባር ነው፡፡
እነዚህ መብቶች በማረምያ ቤት ያሉ እስረኞች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በመሆናቸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ገደብ ሊደረግባቸው የሚችለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻ ከመሆኑ አንጻር የፍርድ ቤቶቹ መዘጋትን ከሕገ መንግሥቱ እና በሌሎች ሕጎች ከተሰጡ ሥልጣኖች አንፃር መመርመር የግድ ያስፈልጋል፡፡
በፍርድ ቤቶች ያለው የፍርድ ሒደት የታገደው ክብርት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. እና መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት “መግለጫ” ነው፡፡ መግለጫው በሕግ ያለው ደረጃ እና አስገዳጅነት ምንድን ነው? የሚለው አከራካሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፕሬዚዳንቷ በመግለጫው ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት ፍርድ ቤቶችን በከፊል የመዝጋት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር ነው፡፡
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር የሚባል ግልጽ የሆነ በሕግ የተዘረጋ አደረጃጀት የለም፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 16 መሠረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በጋራ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነት የተለያዩ ውሳኔዎችን የሚሰጡበት አሠራር አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 31 እና ተከታዮቹ መሠረት የተለያዩ ሥልጣኖች ያሉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ የሚባል አደረጃጀት አለ፡፡ በነዚህ በሁለቱም አደረጃጀቶች ችሎቶችን በከፊል ለመዝጋት ሥልጣን የተሰጠው አካል የለም፡፡
ፍርድ ቤቶች በከፊል የተዘጉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሚያዝያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ከመታወጁ በፊት ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፍርድ ቤቶቹን መዘጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊትና በኋላ ብለን ለይተን ብንመለከተው ሁለት ገጽታ ያለው መሠረታዊ ስህተት እናያለን፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት ፍርድ ቤቶችን በከፊል የመዝጋቱ ተግባር በማረሚያ ቤት ያሉ እስረኞች ባሏቸው መሠረታዊና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶቻቸው ላይ ገደብ የሚያደርግ ተግባር ከመሆኑ አንፃር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልታወጀበት ሁኔታ በእስረኞች ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ ገደብ የሚያደርግ ውሳኔ መስጠቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ ተግባር ሆኖ እናየዋለን፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላም ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብቶች ላይ፣ ገደብ የተደረገባቸው መብቶች የትኞቹ እንደሆኑና በምን መጠን ገደብ እንደተደረገባቸው የሚወሰነው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ብቻ መሆኑ እየታወቀና በዚህ መሠረት የወጣው ደንብ በእስረኞቹ የመዳኘትና የፍርድ ሒደት መብት ላይ ገደብ አለማድረጉ ግልፅ ሆኖ ባለበት ሁኔታ፣ በደንቡ ገደብ ባልተደረገባቸው መብቶች ላይ በራስ ሥልጣን ገደብ አድርጎ፣ ታራሚዎች በሚደረግላቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ መብት እንዳይጠቀሙ ማገድም መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡ የችሎቶች በከፊል መዘጋት የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ወይም ለመገደብ ከሚኖረው ጥቅም አንፃርም ሊመዘንና ሊመረመር ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ችሎቶች በከፊል የተዘጉበትን ምክንያት ስንመለከት ትክክለኛውን መረጃ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መግለጫ ላይ በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለችሎቶቹ በከፊል መዘጋት ምክንያት ያደረገው፣ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በሽታ ለመከላከል በሕክምና ባለሙያዎች የተሰጠው ምክር አካላዊ መራራቅን የሚጠይቅ በመሆኑና አሁን ባሉት ችሎቶች ይህን የሕክምና ባለሙያዎች ምክር ማስጠበቅ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ ጸሐፊው ለሁሉም ችሎቶች በቂ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮችን ሥጋት፣ ምክንያታዊ ሥጋት መሆኑን በትክክል ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን “የጠቅላይ ፍርድቤት አመራሮች የእስረኞችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ከማገድ በተሻለ፣ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውምወይ?” የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረው ችግር አካላዊ ርቀቶችን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ችሎት ውስጥ የሚገቡት ተከሳሾች መጠን እና አቀማመጣቸውን እንዲሁም የዳኞችን አቀማመጥ በማስተካከል በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ችግር ነው፡፡ በተለይ አብዛኛዎቹ የፍትሐ ብሔር ችሎቶች በተመሳሳይ ዝግ በመሆናቸው እነዚህን አዳራሾችም መጠቀም ይቻላል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ከመዘጋታቸው በፊት ባሉት ቀናት በዚህ ሁኔታ አስተናግዶናል፡፡ ይህን ተሞክሮ በመውሰድና ሁሉም ችሎቶች ይህ ተሞክሮ የጎደለውን ሞልተውና አስተካክለው ከችሎታቸው ልዩ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣምም አድርገው የፍርድ ሒደቱን በማስቀጠል የእስረኞችን ችግር በቀላሉ መፍታት ይቻል ነበር፡፡ ሌላው እና ፈፅሞ ትኩረት የተነሳው ነጥብ በኮሮና ምክንያት የፍርድ ሒደቱ ተቋርጦ አንድን ሰው በእስር ላይ እንዲቆይ የማድረግ ተግባር ሕጋዊነት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው በእስር ላይ እንዲቆይ ከተደረገ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ ብዙ መብቶቹ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተገድበው የሚገኙ በመሆኑ፣ የተፋጠነ ፍርድ የማግኘት መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የአንድን እስረኛ የፍርድ ሒደት አግዶ ያለምንም የፍርድ ሒደት በእስር እንዲቆይ ማድረግ፣ በማናቸውም መመዘኛ ሕጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን የኮሮና ቫይረስ በሽታን ሥርጭት ለመከላከል ከሚከናወን ተግባር አንጻር ስንመለከተውም፣ የፍርድ ሒደቱን ከማገድ ውጭ ያሉ የመፍትሔ አማራጮችን መከተል እየተቻለ በእስረኛው ላይ ሊመለስና ሊካስ የማይችል የፍርድ ሒደትን የማገድ አማራጭ መከተል ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ በማናቸውም ምክንያት ይህ በሽታ እስኪወገድ ድረስ የፍርድ ሒደቱን ማስቀጠል የማይቻል ከሆነ፣ ለዚሁ ልዩ ሁኔታ አግባብነት የሚኖረውን ሕግ በማውጣት ወይም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣንን በመጠቀም፣ የበሽታው መወገድ እስኪረጋገጥ ድረስ ክሱን በማቋረጥ እስረኞቹ ከእስር እንዲለቀቁ ማድረግ፣ በሽታው መወገዱ ሲረጋገጥ ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሰው የፍርድ ሒደታቸው የሚቀጥልበትን ሁኔታ በመፍጠርና ለዚህም እስረኞቹ ተገቢውን ዋስትና እንዲሰጡ በማድረግ ከእስር በመልቀቅ የበሽታውን ሥርጭት መከላከልም ሆነ የእስረኞችን መብት ማስከበር ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ሥርጭትን የመከላከል ተግባርን በሌላ በኩል ደግሞ የእስረኞችን ሕገ መንግሥታዊ መብትን አክብሮ ማስከበርን ሚዛን ላይ አስቀምጦ በማየት፣ የእስረኞች መብት በተከበረበት እና በእስረኞች መብት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል የሚቻልበትን ፍትሐዊ የመፍትሔ አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በማንኛውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላል፡፡