በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ይኖር የነበረው ዕድሜ ጠገቡና ዝነኛው ዝሆን፣ ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ሕይወት ማለፉን የፓርኩን ኃላፊ ጠቅሶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
“ሹሉሬ” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ዝሆን የሞቱ መንሥኤ እርጅና መሆኑን ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ሚዲያው ገልጿል፡፡
ሟቹ ዝሆን አድፍጦ የሚያጠቃ ግዛቱን ያስጠብቅ ስለነበረ በኮንታኛ ቋንቋ “ሹሉሬ” የሚል ስም በኅብረተሰቡ እንደተሰጠው ይወሳል፡፡ ሹሉሬ ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠረ ይገመታል፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ “የአፍሪካ ዝሆን” ተብሎ ከሚታወቀው ዝርያ ባለፈ፣ 37 ዓይነት አጥቢ አጥቢ እንስሳትና 237 ዓይነት የአዕዋፋት ዝርያ ያሉበት ነው፡፡ የአፍሪካን ዝሆንና ጎሽን ለማየት ምርጡ ቦታ ጨበራ ጩርጩራ ነው በማለት የጉዞ ማስታወሻ የውጭ ጸሐፊዎች ጽፈውለታል፡፡
የማዜን እና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮችን ክልል ለመወሰን፣ በመስከረም 1997 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በወጣው ድንጋጌ እንደተጠቀሰው፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ በዳውሮ ዞን ኢሠራና ቆጫ ወረዳዎችና በኮንታ ልዩ ወረዳ ያለውን 119,000 ሄክታር ቦታ ይሸፍናል፡፡