በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር በመተባበር “ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ዓውደ ጥናት (ዌብናር ሲምፖዚየም) ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡
ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ዓውደ ጥናቱ የሚካሄደው በዙም በጉግል ስብሰባ መስመሮች ሲሆን፣ ተባባሪዎቹ ምሁራን የተወጣጡት ከቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሂብሪው ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከባዛሌል አካዴሚ ነው፡፡
ቀዳሚው ዓውደ ጥናት የሚጀመረው ረቡዕ ሰኔ 10 ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት ከቴልአቪቭ ሲሆን፣ ጥናት አቅራቢዎቹ ሃጋይ ኢርሊች (ፕሮፌሰር) እና አንበሴ ተፈራ (ዶ/ር) ከከቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ፣ ቤኒ ፉስት (ዶ/ር) ከሂብሪው ዩኒቨርሲቲ፣ ሮን ግሮስ (አርክቴክት) ከባዛሌል አካዴሚ ናቸው፡፡
ዓውደ ጥናቱ ከአዲስ አበባ የሚካሄደው ረቡዕ ሰኔ 30 ቀን ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ከክርስቶስ ልደት 1000 ዓመታት በፊት በንግሥተ ሳባ (ማክዳ) ዘመን የተጀመረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ደብረ ሥልጣንን (ዴር ሡልጣን) ጨምሮ በርካታ ይዞታዎች እንዳሏት ይታወቃል፡፡