ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ የፊታችን እሑድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ማለዳ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡ ግርዶሹ በአፍሪካ ዕምብርት ሲጀምር በጨረቃ ጥላ ሥር የሚያልፉት አገሮች ኮንጎ ዴሞክራቲክ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ኤርትራን ሲሆኑ፣ ሌሎች አካባቢዎች የሚያዩት ከፊል ግርዶሽ ነው፡፡
ቀለበታዊው ግርዶሽ የሚታየው ጨረቃ በፀሐይና በምድር መካከል ስትሆንና ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ ብርሃን መስጠት ሳትችል በሚፈጠር ክስተት ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ተጣጥማ በምትታይበት ወቅት በፀሐይ ዙርያ ሆና ቀለበታዊ ቅርፅ ታሳያለች፡፡
በኢትዮጵያ ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምሥራቅ የሚታየውና የቀለበት ቅርፅ እንደሚኖረው የተገለጸው የፀሐይ ግርዶሽ፣ ከጠዋቱ 12፡45 እስከ እኩለ ቀን (6፡33) እንደሚቆይና ከረፋዱ 3፡40 ደግሞ ለ38 ሴኮንዶች ጨለማ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በተለይም በከፊል ጎጃም፣ ጎንደርና ወሎ የሚከሰት ሲሆን ከሌሎች ቦታዎች በተለየ መልኩ በላሊበላ ከተማ ድቅድቅ ጨለማ እንደሚከሰት ተገልጿል፡፡
ቀለበታዊው ግርዶሽ ከአፍሪካ ማዶ የመን፣ ኦማን፣ ፓኪስታንና ህንድ ቻይና እንደሚከሰትና ፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ ያበቃል ተብሏል፡፡
ቀለበታዊው ግርዶሽ የሚታይባት ጁን 21 (ሰኔ 14)፣ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ፀሐይ ከምድር ወገብ በጣም ከምትርቅበት ቀናት አንዱ ስትሆን ፀሐይ ለረዥም ሰዓት ትታያለች፡፡ ይህም በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ባሉ አገሮች የበጋ ወቅት መጀመርያ ሲሆን፣ ከምድር ወገብ በሚገኙ አገሮች ይፋዊ ባይሆንም የክረምት ወቅት ይጀምርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት ግን ክረምት በይፋ የሚገባው ወቅቱን ከፀደይ የሚረከበው ሰኔ 26 ቀን ነው፡፡
ኅብረተሰቡ ግርዶሹን ለማየት በአንድ ላይ እንዳይሰባሰብ ርቀቱንም ጠብቆ በየቤቱና በየአካባቢው ማየት እንደሚገባውና በዓይንም ሆነ በኦፕቲካል መሣርያዎች ወደ ፀሐይ ቀጥታ መመልከት ዓይንን ሊያጠፋ እንደሚችል ያሳሰበው የአፍሪካ የሥነ ፈለክ ማኅበር፣ ግንዛቤን የሚፈጥሩ ፖስተሮችና የተለያዩ ኅትመቶች ከማዘጋጀቱ ባለፈ ነፃ የአንድሮይድ መተግበሪያንም አማርኛን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፡፡
አኅጉራዊው ማኅበር ግርዶሹ የሚታይባቸውን አገሮች በካርታው ባመላከተበት መተግበሪያው ውስጥ የግርዶሽ ሒደቱን መጀመርያና ማለቂያ ጊዜ፣ የግርዶሹ መጠን፣ የቆይታ ጊዜና የመሳሰሉትን የአንድ ስፍራ/ቦታ መረጃ በአንድ መስኮት ላይ ያሳያል፡፡ እንዲሁም በተመረጠው ቦታ ያለውን ከፍተኛውን የግርዶሹን ምስል መተግበሪያው ከማመልከቱ በተጨማሪ ስለ ግርዶሽ ምንነት እንዲህ አካቷል፡፡
የፀሐይ ግርዶሾች
የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሐይና መሬት መሃከል ስትገባ ይከሰታል፡፡ የሦስቱ አካላት የተለያየ አቀማመጥ የተለያዩ ግርዶሾችን ይሰጣል፡፡ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው ጨረቃ ፀሐይን በግርዶሹ ሒደት ወቅት ለጥቂት ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ ስትሸፍናት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ጨረቃ ልክ በፀሐይና በእኛ መሐከል ትሆናለች፡፡ ከፊል ግርዶሽ የሚሆነው ደግሞ በግርዶሹ ሒደት ውስጥ የፀሐይ የተወሰነው አካል በጨረቃ ሲሸፈን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ጨረቃ በተወሰነ መልኩ በፀሐይና መሬት መካከል ትሆናለች፡፡ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ የሚፈጠረው ደግሞ የጨረቃ መጠኗ ከፀሐይ አነስ ሲልና አቅጣጫዋ ግን በትክክል በፀሐይና መሬት መካከል ሲሆን የሚከሰት ነው፡፡ በግርዶሹ ሒደት ውስጥ ፀሐይ በጨረቃ ዙርያ ቀለበት ሠርታ ትታያለች፡፡
ጨረቃ በመሬት ዙርያ ያላት ምህዋር ትክክለኛ ክብ ሳይሆን ሞላላ ነው፡፡ ጨረቃ ከመሬት ርቃ የምትገኝበት ርቀት ለመሬት ስትቀርብ ካላት ርቀት በ12% ይለያል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በሰማይ ላይ የሚታየው የጨረቃ መጠኗም በ12% ልዩነት አመጣ እንደ ማለት ነው፡፡ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ ከመሬት ርቃ ባለችበት ወቅት የሚከሰት ከሆነ ጨረቃ በመጠን ስለምታንስ በግርዶሹ ሒደት ወቅት ፀሐይን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አትችልም፡፡ ስለዚህ በግርዶሹ ሒደት ውስጥ ፀሐይ በጨረቃ ዙርያ የእሳት ቀለበት ሠርታ የምትታይ በመሆኑ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ በመባል ይታወቃል፡፡
የግርዶሹ አራት ዕርከኖችን እንደሚከተለው በመተግበሪያው ተገልጿል፡-
- የመጀመርያው ንኪኪ(C1): የጨረቃ ጠርዝ ከፀሐይ ጠርዝ ጋር ሲነካካ የከፊል ፀሐይ ግርዶሽ መጀመርያው ነው፡፡
- ሁለተኛው ንኪኪ(C2): ይህ ንኪኪ ቅጽበታዊ የቀለበታማና የሙሉ ፀሐይ ግርዶሽ የሚጀምርበት ነው፡፡
ከፍተኛ ግርዶሽ፡ ጨረቃ የፀሐይን መጠነ ሰፊ አካል በከፍተኛ ሁኔታ የምትሸፍንበት ነው፡፡
- ሦስተኛ ንኪኪ(C3): ቅጽበታዊ የቀለበታማና የሙሉ ፀሐይ ግርዶሽ የሚያበቃበት ነው፡፡
- አራተኛ ንኪኪ(C4): የጨረቃ የኋላ ጠርዝ ከፀሐይ ዲስክ ጋር መደረቡን የሚላቀቅበትና ግርዶሹ የሚያበቃበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ፣ በላሊበላ ከተማ የሚታየውን ግርዶሽ ለማየት ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና ቱሪስቶች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ባይመጡም፣ ኢንስቲትዩቱ ከፌዴራልና ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ከኮማንድ ፖስት ጋር በመነጋገር በላሊበላ ከተማ ዝግጅት ሊኖር እንደሚችል ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ ግርዶሹ በሚከሰትበት ጊዜ ያለ አጋዥ መሣሪያ በባዶ ዓይን ማየት ዓይንን ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ መክሯል፡፡
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዐረፍተ ዘመኖች የፀሐይ ግርዶሽ ታይቶ እንደነበር በባሕረ ሐሳብ መጻሕፍት ተመዝግቧል፡፡

የጥንቃቄ መመርያ
- በባዶ ዓይን በፍፁም ወደ ፀሐይ አትመልከቱ!
- ዓይንን ሙሉ ለሙሉ ስለሚያጠፋ በቴሌስኮፕ፣ በርቀት መነፅር፣ በሌንስና በመሳሰሉት በፍፁም ወደ ፀሐይ እንዳይመለከቱ፤የራጅ ማያ ፊልሞችና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች ግርዶሽን ለማየት በፍፁም ከአደጋ ነፃ መሣርያዎች አይደሉም፡፡
- ከአደጋ ውጭ የሆነው ግርዶሹን የማያ መንገድ የፀሐይን ብርሃን ወረቀት ላይ እንዲያርፍ አድርጎ ከወረቀቱ ላይ ማየቱ ነው፡፡ ይህንን በቤታችን ውስጥ ሆነን የምናይበት መንገድ ቀጥሎ ባለው ክፍል እንደተጠቀሰው ይሆናል፡፡
- የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጠ የግርዶሽ መመልከቻ መነፅሮችን በመጠቀም ግን የፀሐይን ግርዶሽ መመልከት እንችላለን፡፡ እነዚህ መነጽሮች ከሌሎች የተለዩ ሲሆኑ የሚታየውን የፀሐይ ብርሃን እስከ መቶ ሺሕ ጊዜ የሚቀንሱ ሲሆን፣ አልትራቫዮሌትና ኢንፍራሬድንም እንዲሁ ይቀንሳሉ፡፡
ራስን ከአደጋ በመጠበቅ ግርዶሹን ለማየት የሚረዱ መንገዶች
- አንደኛው መንገድ፡ እጅግ አነስተኛ ሽንቁር ቀዳዳ (pin-hole) መጠቀም ሲሆን፣ ይህም ከየትኛውም ስፍራ በቤት ውስጥ ሆነን በጣም በተሻለ መልኩ የምንጠቀመው ዘዴና በእኛ ምናባዊ ዕይታ ላይ የሚወሰን ነው፡፡
- ሁለተኛው መንገድ ፡ ቴሌስኮፕን ወይም አጉሊ መነጽር (ባይናኩላር) መሣሪያን በመጠቀም የፀሐይን ምስል በቅርብ ርቀት ከመሣሪያው ሲወጣ (ፕሮጄክሽን) በማሳያ በማድረግ የምናይበት መንገድ ነው፡፡
የሽንቁር ቀዳዳ (pin-hole) ዘዴ
- በጫማ ማስቀመጫ ካርቶን ወይም ወረቀት ላይ ያዘጋጃችሁትን ሽንቁር ቀዳዳ በፀሐይ ብርሃን በኩል በመደቀን፣ ከፀሐይ በተቃራኒ በኩል ባለው የካርቶን (የጫማ ማስቀመጫ) ጠርዝ የፀሐይ ምስልን መመልከት ትችላላችሁ፡፡
- የዛፍን ተፈጥሯዊ የሽንቁር ቀዳዳን ወይም ክፍተትን መጠቀም ሌላው መንገድ ነው፡፡ ዛፎች ካለምንም ወጪ ከ100 በላይ ሽንቁር ቀዳዳዎችን እንድንጠቀም ያስችሉናል፡፡ ከዛፍ ሥር በሚገኘው መሬት ላይ ብዛት ያላቸውን የፀሐይ ምስሎችን መፍጠር ይቻላል።