ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው ታሪካዊው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ቢያንስ ሁለት ቀሪ ዓመታት ከፊት ቢኖሩም ዘጠነኛ ዓመቱን የያዘበት የዘንድሮው ዓመት ግን ለኢትዮጵያ የምጥ ያህል የከበዳት ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነው። አንድም በግድቡ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የውኃ ሙሌት መጀመር ጥሪቱን አሟጦ ግድቡን እየገነባ ላለው እና የግድቡን የመጀመሪያ ብርሃን ለናፈቀው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የማብሰር ጉጉት ነው። ሌላኛው ግን ከዚህ ፍላጎት በተቃራኒ የቆመው የታችኞቹ አባይ ውሃ ተጋሪ ሀገራት የሆኑት ግብፅ እና ሱዳን የመጀመሪያው ምዕራፍ የውሃ ሙሌት ጉዳት እንደማያደርስባቸው መተማመኛ ሳያገኙ እንዳይጀመር የሚያሰሙት ጩኸትና ሙሌቱ እንዳይጀመር የሚያደርጉት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በዘንድሮው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ አይሎ ፈተና መጋረጡ ነው። የሕዳሴ ግድቡ የሚገነባው ግብፅ ለክፍለ ዘመናት በብቸኝነት በምትጠቀምበት እና ሌሎች ሀገራትን በተለያዩ ስልቶች ተብትባ እንዳይጠቀሙ ብቻ ሳይሆን የመጠቀም ጥያቄ ጭምር እንዳያነሱ ባደረገችበት በአባይ ውኃ ላይ የሚገነባ ጭምር መሆኑ ይታወቃል።የጋራ በሆነው የተፈጥሮ ሀብታቸው ሌሎቹ ሀገራት የመጠቀም ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳን እንዳይችሉ ለማድረግ ግብፅ የውጭ አበዳሪ ሀገራትን በፖለቲካ ተጽእኖ አስራ በመያዟ እና አበዳሪዎችም ወደዚህ ተቃርኖ ላለመግባት ይህንን ተፋሰስ ለማልማት ለሚቀርብላቸው የብድር ጥያቄ በራቸው ዝግ ነው። ኢትዮጵያም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ስትጀምር ይህንን ሀቅ በመገንዘብ በመሆኑ የግንባታ ወጪውን ሙሉ በመሉ በራሷ አቅም ለመሸፈን ቆርጣ የገባችበት ጉዳይ ነው። ነገር ግን ከግንባታ መዘግየት እና ምዝበራዎች ጋር በተገናኘ ፕሮጀክቱ ሲጀመር የተገመተው አጠቃላይ ወጪ ከ80 ቢሊዮን ብር ወደ 140 ቢሊዮን ብር ከፍብሏል። በርካታ ወጪዎች የሚፈጸሙትም በውጭ ምንዛሪ መሆኑ እና የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ የሆኑት ውስን ዘርፎች በመሆናቸው እንዲሁም ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የኤክስፖርት ንግድ ከታቀደው በታች በከፍተኛ ደረጃ ላለፉት ዓመታት በማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ወጪ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጥዝጣዜ ፈጥሯል። ነገር ግን ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ህዝቦችና በመንግስትም እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚታይ በመሆኑ የግድቡ የወጪ ፍላጎት፤ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ጨምሮ ቅድሚያ እንዲያገኝ በመንግስት ተወስኖ የመጣ ነው። ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለ ግድቡ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሲያብራሩ የተናገሩት ይህንኑ የሚያስረዳ ነው።”ብዙዎች የሕዳሴ ግድቡ ላይ ያለው የዲፕሎማሲ ፈተና ብቻ አድርገው በቁንጽል ይመለከታሉ” ያለት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የግድቡ ግንባታ ብዙ ፈተናወችን በመፍታት እንደሚከናወን፣ ከነዚህም መካከል ዋናው የቴክኒክ ጉዳይን ማስተዳደር ሲሆን፣ ሁለተኛው ፈተና ገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል።ይህንንምሲገልጹ፤ ” የሕዳሴ ግድቡ አፉን እንደከፈተ ጅብ ነው። በየወሩ ዩሮ ካልጎረሱት አይነቃነቅም። እንደሚታወቀው ደግሞ ለዚህ የሚገኝ ብድርም ሆነ እርዳታ የለም ” ብለው ነበር። አክለውም” ኢትዮጵያ ከምታገኘው ሀብት ቅድሚያ ሰጥታ ለዚህ ፕሮጀክት ማጉረስ ካልቻለች በገንዘብ ምክንያት ብቻ የምንፈልገውን ፕሮጀክት በምንፈልገው ጊዜ ላይከወን ይችላል” ብለዋል።የሕዳሴው ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክፍሌ ሆሮ (ኢንጅነር)፤ የግድቡ ሥራ ከተጀመረ አንስቶእንደዘንድሮ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ እንደሌለ ሰሞኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ በሙሉ አቅም በሁሉም አቅጣጫ በሶስት ሽፍት እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራአስኪያጁ፤ አጠቃላይ የግድቡ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ሥራ በሰኔ አጋማሽ ወር 2012 ዓምላይ 87 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል። የብረታብረት ሥራዎቹ ከ31 በመቶ በላይ እንደተከናወኑ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እንዲሁም የተርባይንና የጀነሬተር ሥራዎች አፈጻጸምም ደግሞ 45 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ አሁን ላይ አጠቃ ላይ የግንባታው አፈጻጸም 74 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል።የተደረገው ጥረትም በቅድሚያ ኃይል የማመንጨት ሥራ የሚጀምሩትን በግድቡ ከሚተከሉት አስራ አንድ ተርባይኖች መካከል ሁለቱን ወደ ሥራ ለማስገባት መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ወደዛ የሚያደርሱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተገባደዱ ሲሆን በእቅዱ መሠረትም ለቅድመ ኃይል ማመንጨት አግልግሎት የሚያስፈልገውን ውኃ የመያዝ ሥራ በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ተናግረዋል። የግድቡን የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችው እቅድ እንደተገለጸው በቀጣዩ ሐምሌ ወር መጀመር እና 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በግድቡ ማቆር ነው። እውን ለማድረግ የሚያስፈልገው ዝግጅትም ከሞላ ጎደል ተጠናቋል። ነገር ግን ይህ እውነታ መቅረቡን የተረዳችው ግብፅ፤ ግድቡ ኢትዮጵያ በያዘችው መርሐ ግብር እና የሙሌት እቅድ መሠረት የግድቡ ሙሌት ከተጀመረ የመቶ ሚሊዮን ግብጻውያን ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ እና ብሔራዊ ደህንነቷንም እንደሚፈትን በመግለጽ አቤቱታዋን አጠንክራ በማሰማት ቀላል የማይባል ፈተና ደቅናለች። የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በአሜሪካ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ይሆንኑ አቤቱታቸውን በማሰማት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለጉዳዩ እልባት በመፈለግ የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ባቀረቡት ጥሪ ዲፕሎማሳያዊ ጫናቸውን መጀመራቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ሲሲ ለተመድ ስብሰባ ወደ አሜሪካ በሄዱበት አጋጣሚ ለጉባኤው ከማቅረባቸው ባለፈም አቻቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጋር ያላቸውን የግል እና ሀገራዊ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ጥቅም ግንኙነት መሠረት በማድረግ በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል። ይህንን ተከትሎ በነበሩት ጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል የነበረው የግድቡ ሙሌትን የተመለከተ ድርድር በማቋረጥ አሜሪካ እንድታሸማግል ባቀረበችው ጥሪ መሠረት ድርድሩ ወደ አሜሪካ መሸጋገሩ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት የግብፅን ጥያቄ ተቀብሎ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ወደሚታዘቡት የአሜሪካ ድርድር መሄዱ በበርካታ የኢትዮጵያ ልሂቃን ትችት ዳርጎታል። የዚህ ትችት ምክንያት ደግሞ ግብፅ በሕዳሴ ግድቡ ላይ የምታነሳቸው ጥያቄዎች የቴክኒክ ቢሆኑም በቴክኒክ ድርድር ጥያቄዎቿ እንደማይመለሱ በመረዳት ለዘመናት እንዳደረገቸው ጉዳዩን ባላት የፖለቲካ የበላይነት ለመመለስ በነደፈችው እቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ መግባት የለባትም የሚል ሙግት ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ታላቁ የህደሴ ግድብ ግንባታን የምታከናውነው በሉዓላዊ ግዛቷ እና በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ በመሆኑ፤ እንዲሁም ፍትሀዊ እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ዓለም አቀፍ መርህን በመከተል እስከሆነ ድረስ ግብፅ ውዝግቡን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በጎነጎነችው ሴራ ውሰጥ ኢትዮጵያ ለመግባት መወሰን አልነበረባትም የሚል ነው።
በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ የታዛቢነት ሚና በዋሽንግተን የተጀመረው የሦስቱ ሀገራት ድርድር አራት ወራትን ከፈጀ በኋላ፤ ኢትዮጵያ በድርድሩ ወቅት ባስተዋለችው የአሜሪካ አድሎአዊ ጣልቃገብነት እንዲሁም ከታዛቢነት ወደስምምነት ሰነድ አርቃቂነት ሚናዋን መቀየር ምክንያት ድርድሩን አቋርጣ ወጥታለች። በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ የገጠማቸውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና በተመለከተ ሲናገሩ፤ “የሕዳሴ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ እንደ ዘንድሮ ያለዲፕሎማሲያዊ ፈተና ገጥሞ አያውቅም፤ ይህ የሆነበት ምክንያትም ፕሮጀክቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ከመድረሱ የመነጨነው” ብለው ነበር።ከመስከረም ወር አንስቶ የጀመረው የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የአሜሪካን ጣልቃገብነት አዝሎ ወደ ተመድ የፀጥታው ምክርቤት ባለፈው ሳምንት በድጋሚ አምርቷል።
የሱዳን ሁለት እግሮች
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዘንድሮ ድረስ ሱዳን ግድቡ ከሚያስገኝላት ጥቅም አንፃር በይፋ ስትደግፈው ቆይታለች።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳትም ሆነ ስጋት የለውም” ሲሉ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ዑመር አልበሽር እ.ኤ.አ. በ2013 በይፋ ከመናገር አልፈው የግድቡን ግንባታ በአካል በመጎብኘት የኢትዮጵያ መንግስትን ያበረታቱ ነበር።
በአሁኑ ወቅት የሱዳን የመስኖ ሚንስትር ያሲር አባስ ከጥቂት ወራቶች በፊት ለሱዳን የዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ያንፀባረቁትም ይህንኑ ነው። የሕዳሴ ግድቡ የግንባታ ጥራት፣ የዲዛይን እና የመረጃ ግብአት ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ልዩ ጥንቃቄ እየተገነባ ያለ በመሆኑ ግድቡ ሊሰነጠቅ ወይም ሊደረመስ የሚችልበት ሁኔታ ጨርሶ የለም። የግንባታው የጥራት ደረጃ በሱዳን ከሚገኙት ተመሳሳይ ግድቦችም ሆነ ከግብፁ የአስዋን ግድብ በእጅጉ የተሻለ ነው” ብለው ነበር።የግድቡ እውን መሆን ለሱዳን ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ የውኃ ፍሰት እንድታገኝ እና በዚህም የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ከሚካሄድ የግብርና ልማት ዓመቱን ሙሉ እንድታለማ እንደሚያስችላት ገልጸዋል። በተጨማሪም የአባይ ውኃ ወደ ሱዳን ይዞት የሚመጣው ደለል እንደሚቀር እና ይህም በሱዳን የሚገኙ ግድቦችን በደለል ከመሞላት እንደሚታደግ፣ የውኃ መያዝ መጠናቸው እንዲጨምር እንደሚያደርግ እና የአገልግሎት እድሜያቸውንም እንደሚያራዝም እንዲሁም ሱዳን ከግድቦቿ ደለል ለመጥረግ በየዓመቱ የምታወጣውን 60 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስቀር ባለስልጣናቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲገልጹ ከርመዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ይህ የሱዳን መንግስት አቋም ተቀይሯል።
የወቅቱ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብዱላ ሀምዱክ በዚህ ወር ላይ ለተመድ በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ የግድቡ የውኃ ሙሌትን አሰመልክቶ እየተደረገ ባለው የሦስትዮሽ ድርድር የውኃ ሙሌቱን ብትጀምር በሱዳን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በመግለጽ አሳስበዋል።
በዚህ ግዙፉ መጠን የሚገነባው የሕዳሴ ግድብ በተገቢው ደረጃ ዲዛይን የተደረገ እና በዛው ደረጃ ካልተገነባ እና የውኃ ሙሌቱ ካልተከናወነ በሱዳን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ከግድቡ በታች የሚኖሩ ሚሊዮን ሱዳናዊያን ህይወትን ላደጋ ያጋልጣል” ሲሉ በጻፉት ደብዳቤ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህም ከቀድሞ የሱዳን ባለስልጣናት እንዲሁም አሁን ስልጣን ላይ ከሚገኙት እና ሱዳንን ወክለው ግድቡን በተመለከተ ከሚደራደሩት የመስኖሚንስትሩ አቋሞች የሚቃረን ነው። ጠቅላይ ሚንስት ርአብዱላ ሀምዱክ ለተመድ በጻፉት ደብዳቤ ላይ የሚታየው የአቋም ለውጥ ይህ ብቻ አይደለም። ” የአባይ ውኃ ወደ ሱዳን ይዞት የሚመጣው ደለል ለሱዳን ግብርና ጥሩ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ነው፤ ነገርግን በሕዳሴ ግድቡ ምክንያት ይህ ጥሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያነትን የያዘ ደለል የሚቀር ወይም መጠኑ የሚቀንስ በመሆኑ በሱዳን የግብርና ልማት ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል።በዚህም ሳያበቁ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ የውኃ ሙሌቱን ብታካሂድና ይህንን ተከትሎ ሊወሰድ በሚችል እርምጃም ቀዳሚው ተጎጂ ሱዳን እንደሆነች በመጥቀስ የግብፅን ዛቻዎች የሚያጠናክር አስተያየት በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።ይህ የሱዳን የአቋም ለውጥን ማንፀባረቅ የጀመሩት ጠቅላይ ሚነስትሩ ከጥቂት ወራቶች በፊት ግብፅ የአረብ ሊግ አባል ሀገራትን ሰብስባ ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያን የሚያወግዝ መግለጫ እንዲወጣ ስታደርግ ተቃውመው ራሳቸውን እናሀገራቸውን ያገለሉ መሆናቸው ይታወሳል። ሱዳን በምን ምክንያት አንዴ ወደ ኢትዮጵያ፣ አንዴ ወደ ግብፅ እየረገጠች የአቋሟ ውል ያልታወቀው የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ አዕምሮ እየተመላለሰ ይገኛል። የነዚህ የአቋም መወላወሎች ምክንያት ሱዳን በግድቡ ላይ ካደረገችው ግምገማ የሚመነጭ ሳይሆን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከተወገዱ በኋላ የተቋቋመው የሱዳን የሽግግር መንግስት ወቅታዊ የኢኮኖሚ እናየፖለቲካ ፍላጎቶችን ለመመለስ ቅድሚያ ከሰጠው ፍላጎት የተነሳ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። ከዚህም ጀርባ የአሜሪካ መንግስት በግልጽ እንደሚታይ የሚገልጹት ያነጋገርናቸው ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ተንታኞች በግድቡ የጥራት ደረጃ ላይ ጥያቄ እና ስጋት የተነሳው በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ የታዛቢነት ሚናየነበረው የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ባወጣው መግለጫ እንደሆነ ያስታውሳሉ። በዚህ መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ግድቡን መሙላት እንደሌለባት ሲያሳስብ ከተጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ሱዳን በግድቡ የግንባታ ጥራት ላይ ጥያቄ እና ስጋት እንዳላት የሚገልጽ እንደነበር ይገልጻሉ። በዚህ ወቅትም ሆነ በኋላ በነበሩት ጥቂት ወራቶች ከሱዳን በኩል እንደዚህ ዓይነት ስጋት እንዳልነበር ለዚህ ማስረጃውም ዋና ተደራዳሪው የመስኖ ሚንስተሩ ከአንድ ወር በፊት በሰጡት ቃለምልልስ ላይ እንኳን ስለግድቡ የጥራት ደረጃ ከኢትዮጵያ በላይ አድንቀው እንደተናገሩ በማንሳት ያስረዳሉ። ነገር ግን በአሜሪካ እና በሱዳን መካከል ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ የነበረ ድርድር እንዳለ ከነዚህም መካከል አንዱ አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመሰረዝ ማሰቧን እና ኢኮኖሚዋን መልሳ ለመገንባት እገዛ ለማድረግ ማሰቧን እንደስጦታ ለሱዳን ማቅረቧን ያስረዳሉ።አሜሪካ ሱዳንን አሸባሪዎችን የምትረዳ ሀገር በሚል በመፈረጇ እና ለበርካታ አስርት ዓመታት ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ማእቀብ ውስጥ በመቆየቷ፤ እንዲሁም የደቡብ ሱዳን መገንጠል የሱዳንን የኢኮነሚ መሠረት የነበረውን የነዳጅ ሀብት 75 በመቶ ይዞ በመሄዱ የሱዳን ኢኮኖሜ መንኮታኮቱን ይገልጻሉ። በመሆኑም አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪ መዝገቧ ብትሰርዝ አሁን ያለው የሱዳን የሽግግር መንግስት ላቀደው ኢኮኖሚውን መልሶ የመገንባት እቅድ ሁነኛ እንደሆነ ይገልጻሉ። በዚህ ሳምንት ውስጥም በጀርመን አዘጋጅነት የሱዳን ወዳጆች ጉባኤ እንደሚካሄድ የሚገልጹት እነዚህ ተንታኞች፣ የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር በዚህ ስብሰባ ላይ የሱዳንን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት የ10 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። በመሆኑም የሱዳን የአቋም ለውጥ ኢትዮጵን የሚጎዳ ቢሆንም ከብሔራዊ ጥቅሟ እንፃር ተገዳ የገባችበት እንደሆነ መረጃዎቹ በግልጽእንደሚያሳዩ ያስረዳሉ።
ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የመሄድ አንድምታ
በሱዳን አነሳሽነት በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል በሕዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አስተዳደር ላይ ሰሞኑን ሲካሄድ የነበረው ድርድር በተለይ የግድቡን የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት አስመልክቶ መግባባት የተደረሰበት እንደነበር የተገለጸ ቢሆንም በሌሎች ጉዳዮች በዋናነትም የድርቅ ወቅት ጉዳትን መቀነስ በሚቻልበትና ሦስቱ ሀገራት የሚደርሱበት ስምምነት ይግባኝ የማይቀርብበት ገዢ ማእቀፍ ሊሆን ይገባል እና አይገባም በሚለው የኢትዮጵያ አቋም ምክንያት ተቋርጧል። ይህንን ተከትሎም ግብፅ ዳግመኛ አቤቱታዋን ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ማቅረቧ ታውቋል። ግብፅ ዳግመኛ አቤቱታዋን ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው በተመድ ቻርተር አንቀፅ 34 መሠረት ነው። ይህ አንቀጽ ማንኛውም አለመግባባት ወይም ግጭት የዓለምን ሠላም ሊጎዳ የሚችል ከሆነ ነገሩን መርምሮ አስታራቂ ምክረ-ሀሳብ እንዲያቀርብ ወይም ሌላ የመፍትሔ ሀሳብ እንዲያቀርብ ለፀጥታው ምክርቤት ስልጣን ይሰጣል። ግብፅ ካቀረበችው አቤቱታ በተጨማሪ ሦስቱ ሀገራትን ባላግበባው ጉዳይ ላይ ሱዳንም ተመሳሳይ ቅሬታዋን ለዚሁ ምክር ቤት በዚሁ ወር ያቀረበች በመሆኑ ምክር ቤቱ ጉዳዩን ላለማየት እንደማይችል ገልጸዋል። በዚሁ የተመድ ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረቡትን ጉዳይ መርምሮ አስታራቂ ሀሳብ የመስጠት መብት ያለው ሲሆን ጉዳዩ በዚህ የመፍትሄ ሀሳብ ካልተፈታ እና ነገሩ የህግ ጉዳይን የሚመለከት ከሆነ ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሊመራ እንደሚችል ገልጸዋል። ነገር ግን ይህንን ወደ ፍርድ ቤት የመሄድ አማራጭ ግብፅ እንደማታሸንፍበት ስለምትረዳ እንደማትፈልገው የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኞች፤ የፀጥታው ምክር ቤት ከዛ በመለስ ባለው ስልጣኑ የግድቡ የውኃ ሙሌት ስምምነት ሳይደረስ እንዳይሞላ ሊወስን እንደሚችል ገልጸዋል። ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ የዚህ ምክርቤት ቋሚ እና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ አሜሪካ በመሆኗ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ አሸንፋ ሕዳሴ ግድቡን በእቅዷ መሠረት በመጪው ሐምሌ ወር መሙላት ካልቻለች ደግሞ፤ የቀጣዩ ዓመትን ክረምት መጠበቅ እንደምትገደድ እና ይህ ደግሞ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ላይ የራሱ አሉታዊ አንድምታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከዚህ አንፃርም የአፍሪካ ህብረት ሰሞኑን የሕዳሴ ግድቡ ላይ ሀገራቱን ለማደራደር መወሰኑ እና ሀገራቱም በዚህ መስማማታቸው ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።በአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት አመቻችነት እና ሰብሳቢነት ሦስቱ ሀገራት ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓም ተወያይተው በህብረቱ አደራዳሪነት ልዩነታቸውን በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመፍታት መስማማታቸው ይፋ ሆኖል።ኢትዮጵያም በሁለት ሳምንት ውስጥ የግድቡን ቀሪ ስራዎች አጠናቃ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ማከናወን እንደምትጀምር ገልጻለች።ሀገራቱ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት የአፍሪካ ህብረትን አደራዳሪነት መቀበላቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል የሚሉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ፤ ግድቡን በተመለከተ መግባባት እንዳይደረስ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ግብፅ የግድቡ የውኃ ሙሊትን ከውኃ ክፍፍል ጋር በማስተሳሰሯ በመሆኑ ይህ የግብፅ ጥያቄ ሌሎቹን የወንዙ ተጋሪ የአፍሪካ ሀገራትን የሚመለከት በመሆኑ እና አፍሪካ ህብረትም የህብረቱ አባል የሆኑ ሌሎች ሀገራትን ጥቅም የሚነካ ስምምነት ማመቻቸት ከኃላፊነቱ የሚጣረስ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።በመሆኑም ግብፅ የውኃ ክፍፍልን በዚህ የምታነሳ ከሆነ ፤ ከግብፅ እና ሱዳን ውጪ ሌሎቹ የወንዙ ተጋሪ ሀገራት እ.ኤ.አ. 2010 በኡጋንዳ የፈረሙትን የአባይ ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ (CFA) ተቀብለው እንዲፍርሙ መሞገት እንደሚገባት መክረዋል።ይህ ማእቀፍ የውኃ ክፍፍል ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገርም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ትብብር እንዲፈጠር የሚያስችል የናይል (ዓባይ ) ተፋሰስ ኮሚሽን በአፍሪካ ህብረት ስር እንዲቋቋም የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ትኩረት አድርጋ ልትንቀሳቀስ እንደሚገባ በአጽንኦት መክረዋል።
የፀጥታው ምክርቤት ምክረ ሀሳብን አለመቀበል የሚቻል ቢሆንም፤ ይህንን ለማድረግ ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ እንደ ማእቀብ ያሉ ጉዳዮችን የመሸከም አቅም ሊኖር እንደሚገባ እና ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ወቀት ይህንን የመቋቋም አቅም እንደሌላት ገልጸዋል። ሊመጣ የሚችለውን አጣብቂኝ ለማለፍ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ካሉት አማራጮች መካከል አንዱ እና በተመድ ቻርተርም የተደገፈው፤ ቀጠናዊ የድርድር እድሎችን አሟጦ መጠቀም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን እና የአፍሪካ ህብረትን እንደቀጣይ አማራጭ ልትጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ። የአፍሪካ ህብረት የዚህ ዓመት መርህ የአፍርካ ጉዳዮችን በአፍሪካዊያን የሚል በመሆኑ እና ተመድም ይህንን ላለመቀበል መብት ስለሌለው እንዲሁም አፍሪካዊያን ይህ የግብፅኢ-ፍትሐዊ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ቁስላቸውን ስለሚቆሰቁስ እንደማይቀበሉት፤ ግብፅም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት የተቀዛቀዘ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መውጫ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ይመክራሉ።
በዚሁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ” የኛ ፍላጎት ማደግ ነው። ይህንን ፍላጎታችንን ለማስቆም የሚፈልግ ኃይል ካለ፤ ለኛ መኖርም አለመኖርም ትርጉም የለውም። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በቅን ልቦና ማየት ከሁሉም ወገኖች ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡