በወርኃ ግንቦት ከዓመት በፊት “ከኔሴት” የሚባለው የእስራኤል ፓርላማ አዲስ የተመረጡ የምክር ቤት አባላትን ቃለ መሐላ ለማስገባት ተሰብስቧል፡፡ እንደራሴዎቹና ታዳሚ እንግዶች ወደ አዳራሽ እየዘለቁ ነው፡፡ ከሚገቡት መካከል ኢትዮጵያውያት ይሁዲዎች በባህል አልባሳት ተውበውና ተጊጠው በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ከነርሱም መካከል በዕድሜ ገፋ ያሉ አንዲት እናት ዘመናዊ ከዘራ ይዘው ዋናውን በር አልፈው ሊገቡ ሲል አንድ ከአርባ ዓመት ዕድሜ ያልደረሱ፣ አርባ ፈሪ ላይ ያሉ ወጣት ተንደርድረው ሄደውና በርከክ ብለው የእናቲቱን እግር ይስማሉ፡፡ እናቲቱም አንስተው የወጣቱን ጉንጮች ይስማሉ፡፡ የእናታቸውን ወ/ሮ የንጉሥነሽ እሸቴን እግር የሳሙት ወጣት፣ ከትውልደ ኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎች ሁለተኛው የፓርላማ አባል ሆነው የተመረጡት አቶ ጋዲ ይባርከን ናቸው፡፡

አቶ ጋዲ በየጊዜው መገለልና አድልዎ የሚደርስባቸው ቤተ እስራኤሎችን ከመከራ ለመታደግና በእኩልነትና በፍትሕ በአገራቸው መኖር እንዲችሉ በመሟገት የሚታወቁ ስመ ጥር የእስራኤል ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ከኮሌጅ ሕይወት እስከ ሥራ ስምሪት በነበራቸው ጉዞ የወገናቸውን ክብር ለማብሰር ያደረጉት ትግል ጎልቶ ይወሳል፡፡ አድናቆትም አክብሮትም አግኝተውበታል፡፡
የብሉ ኤንድ ዋይት ፓርቲን ወክለው ለፓርላማ በመመረጣቸው ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ እናታቸው እንዲገኙላቸው ከማድረግ ባለፈ ቃል የማይገልጸውን (በእርሳቸው አገላለጽ) እናታቸው ያደረጉላቸውን ውለታ እግራቸውን በመሳም ለመግለጽ የወደዱት፡፡ “የርሷ ውለታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ በትንሹ ላደርግ የምችለው እግሯን መሳምና መባረክ ነው፡፡” ይህ ድርጊታቸው ብዙዎቹን እንደራሴዎች አስደምሟል፡፡ የአገሪቱ ሚዲያዎች በቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ በኅትመት ሥርጭታቸው ዓቢይ ዜና አድርገውታል፡፡
በእስራኤል ታሪክ በእምነት ጭምር የሚታወቀው ሕግ ከአሠርቱ ትዕዛዛት አንዱ “እናትና አባትህን አክብር” የሚለው ነው፡፡ በወቅቱ እንደተገለጸው አቶ ጋዲ “የእናታቸውን እግር ስመው ሲነሱ ሁሉም ናቸው ያከበሯቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩም አመስግነው ነው የተናገሩት፡፡” …ለዘመናት የተረሳውን ባህል እዚህ ካሉት ቤተ እስራኤል ኢትዮጵያውያን የተማርነው ትልቁ እሴት ነው የሚልም ድምፅ ተሰምቷል፡፡
ይህ ድርጊት በተፈጸመ በዓመቱ፣ ብሉ ኤንድ ዋይት ፓርቲን ትተው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታኒያሁ የሚመሩትን ሊኩድ ፓርቲ የተቀላቀሉት አቶ ጋዲ፣ በተቋቋመው የአንድነት መንግሥት ካቢኔ ውስጥ የደኅንነት ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል፡፡ እሳቸው ብቻ አይደሉም ለከፍተኛ ሹመት የበቁት፤ ሌላዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ቤተ እስራኤል ወ/ሮ ፒንና ታማኖ እሸቴ “የመጀመርያዋ ጥቁር ሚኒስትር” ያሰኛቸው የስደተኞች ጉዳይ መሥርያ ቤትን እንዲመሩ በመሾማቸው ነው፡፡ የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ይሁዲዎች መሾም ይበልታን አስገኝቷል፡፡
በእስራኤል የመንግሥትነት ታሪክ ከሰባት አሠርታት ጥቂት እልፍ ባለ ጉዞዋ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ ትውልደ ኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎችን ለከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ያበቃ ድርጊት የተፈጸመበት ነውና፡፡
ሁለቱም ሹመኞች የእስራኤል ፓርላማ (ከኔሴት) አባላት ናቸው፡፡ ሁለቱም በሕፃንነታቸው ወ/ሮ ፒንና በዘመቻ ሙሴ በ1977 ዓ.ም.፣ አቶ ጋዲ በዘመቻ ሰሎሞን በ1983 ዓ.ም. እስራኤል ባካሄደችው ተልዕኮ በሱዳንና በኢትዮጵያ በኩል ከተጓጓዙት በዓሥር ሺዎች ከሚቆጠሩ ቤተ እስራኤሎች መካከል ይገኙበታል፡፡
ወ/ሮ ፒንና ታማኖ እሸቴ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳሉ ከተወለዱበት ጎንደር አካባቢ ከወላጆቻቸው ጋር በእግር ተጉዘው ሱዳን ገብተው ከዚያም ወደ እስራኤል የተሻገሩ ሲሆን፣ በሕግ ትምህርት ተመርቀዋል፡፡ በእሥራኤል የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚደንት ሆነውም ነበር፡፡ በፖለቲካ ሕይወታቸው የብሉ ኤንድ ዋይት ፓርቲ አባል ሲሆኑ በ2011 ዓ.ም. የመጀመርያዋ ሴት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ያሰኛቸውን የእሥራኤል ምክር ቤት አባል ሆነው መመረጣቸው ነው፡፡ ቀደም ሲል በ“ቻናል 1” ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበሩት ወ/ሮ ፒንና ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡
ከሦስት አሠርታት በፊት የስምንት ዓመት ዕድሜ ላይ ሳሉ ከትውልድ ቦታቸው ደባርቅ አካባቢ ተነስተው በዘመቻ ሰሎሞን ከወላጆቻቸው ጋር ወደ እስራኤል ያቀኑት አቶ ጋዲ ይባርከን፣ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ በብሔራዊ አገልግሎት የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ለስድስት ዓመት ያገለገሉ ሲሆን እስከ ሻለቃነት ደርሰዋል፡፡

የኮሌጅ የተማሪዎች መማክርት ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ጋዲ መገለልና አድልዖ የሚደርስባቸው ቤተ እስራኤላውያን ወገናቸውን ለመታደግ ተሟጋች/አክቲቪስት በመሆን ትግሉን መምራቱን ለአፍታም ቸል ሳይሉ የዘለቁ ናቸው፡፡
ሪፖርተር መጽሔት እኒሀን ባለታሪክ ለማግኘት ባደረገው ጥረት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባመቻቸለት መሠረት አቶ ጋዲን በቴሌፎን አገኘናቸውና ለአንዳፍታ አወጋንና እንዲህ አቀናበርነው፡፡
የአቶ ጋዲ ማንነት
በያኔው አጠራር በጎንደር ክፍለ ሀገር በስሜን አውራጃ ደባርቅ ሰላምጌ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ምቃራ መንደር በ1973 ዓ.ም. ተወለድሁ፡፡ አባቴ አቶ እሸቴ ይባርከን እናቴ ወ/ሮ የንጉሥነሽ እሸቴ ይባላሉ፡፡ ወላጆቼ ከወለዷቸው 17 ወንድና ሴት ልጆች የመጨረሻው ልጅ ነኝ፡፡ የአማርኛ ስሜ ደስታው እሸቴ ሲሆን፣ ጋዲ የሚለውን ስም ያገኙት ከ12 የእስራኤል ነገዶች አንዱ ከሆነው ጋድ [የዕብራይስጥ ትርጉሙ መልካም ዕድል] ነው፡፡ የስምንት ዓመት ሆኜ እስራኤል ከመጣሁ በኋላ ትምህርት ቤት ገብቼ 12ኛ ክፍል ጨረስሁ፡፡ በውትድርና አገልግሎት ለስድስት ዓመት በቆሁበት ምርጥ ኮማንዶ ሆኜ እስከ ሻለቃነት ደርሻለሁ፡፡ ኮሌጅ ገብቼም በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝቻለሁ፡፡
የቤተ እስራኤል መብት ተሟጋችነት
በኮሌጅ እየተማርሁ እያለሁ የቤተ እስራኤልን መብት ለማስከበር በኮሌጅ ምክትል ሊቀ መንበርነት ብዙ ሰላማዊ ሰልፍ ሳደርግ ነበር፡፡ አክቲቪስት መሆኔ የኅብረተሰቡን መብት ለማስከበር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አትንኩን እንላለን፤ በዚህ የተነሳ ወደ ፖለቲካው በመግባት በ2009 ዓ.ም. የቤንያሚን ኔታንያሁን ሊኩድ ፓርቲን ተቀላቀልኩ፡፡ ግቤ የወገኔን መብት ማስከበር እንጂ ሥልጣን ፍለጋ አይደለም፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ አምሳደሯን ቀይሬ እንድሾም አቅደውኝ ነበር፡፡ እምቢ አልሁ፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት መሪዎቻችን ቤተ እስራኤል መብት እንደ ሌሎቹ ራባኖች እንዲከበር ስለምፈልግ ነው፡፡ አርባ ዓመት የወሰደ ትግል ነውና፡፡ እኔ በዚህ 18 እና 20 ዓመት በምመራው ትግል የነርሱ መብት ካልተከበረ በማለት ሰላማዊ ሠልፍ እናደርግ ነበር፡፡ ሥልጣን እንስጠውና ትግሉን ይተው ሲሉ ሹመቱን ተውኩት ከግማሽ ዓመት በኋላ የሃይማኖት መሪዎችን መብታቸውን አስከበርሁ፡፡
የሁለት ፓርቲ ጉዞ
አቶ ጋዲ ለአጭር ጊዜ የቆዩበትን ገዥ ፓርቲ ሊኩድ ትተው በጦር ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ከሚመራው አዲሱ ብሉ ኤንድ ዋይት ፓርቲ ተቀላቀሉ፡፡ በተለያዩ ነገሮች ከፓርቲው ጋር ስላልተስማሙ አልቀጠሉም፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ሽማግሌ ልከው ታረቅን ወደ ሊኩድ ፓርቲ ተመለስሁ፡፡ ኅብረተሰቡም እኔን ደግፎ መጣ፣ በወገኔ ለዚህ ሥልጣን በቃሁ፡፡ ሊኩድ እኔ ሜናሂም ቤጊን፣ ጎልዳ ሜይር የነበሩበት ፓርቲ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነትና እስራኤላዊነት
የእስራኤልና የኢትዮጵያ ግንኙነትና ፍቅር ሰው ሊቆርጠው አይችልም እግዚአብሔር የፈጠረው እስከሆነ ድረስ የሰው ልጅ ፍቅሩን እያዳበረና የበለጠ እየገለጸ ለሚመጣው ትውልድ ድልድይ ከመሆን በስተቀር ሰው ይቆርጠዋል ብዬ አላምንም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እኛ ቤተ እስራኤሎች ወደ ኢትዮጵያ በመጀመርያው ቤተ መቅደስ ስንመጣ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው በንግሥተ ሳባና ሰሎሞን ዘመን ከ12 ነገዶች ተወጣጥተን የመጣን ነን፡፡ መመለሳችንም በትዕዛዝና በሃይማኖት እግዚአብሔር በነቢያት በኩል ብሎት የተፈጸመ ነው፡፡ ‘አንድ ቀን ትመለሳላችሁ’ ብሎም በመጽሐፍ ቅዱስ ተነግሯል፡፡ ኢትዮጵያ የእኛ፣ የአባቶቻችን፣ የአያት ቅድመ አያቶቻችን ርስት ናት፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትና ከመምጣቱ በፊት በብሉይ ኪዳን ስታምን የኖረች ናት፡፡ እኛ ወደ እስራኤል የመጣንበት ምክንያት የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ያለው ቃል በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ ኢትዮጵያ አስከፍታን አይደለም፡፡ አገራችንን ለቀን የወጣነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም በየትኛውም እምነት የሚያምነው ሁሉ ወገናችን ነው፡፡ ወደ እስራኤል ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በጸሎትና በሐሳብ የምናነሳቸው ወገኖቻችን አገር ናት፡፡ እኔም አባቶቼና እናቶቼ የሰጡኝን የአገራችን ፍቅር እንደ እስራኤላዊነቴ ባለሁበት ሥልጣን ወገኔነ ዞር ብዬ ለማየት ዕድል ካለኝ ለመርዳት ወደ ኋላ አልልም፡፡

ምክትል ሚኒስትርነት
የተሾምኩበት መሥሪያ ቤት በእስራኤል መንግሥት አሉ ከሚባሉት ሁለት ሦስቱ አንዱ ነው፡፡ የአገር ደኅንነትና ፖሊስን በተለያዩ ሁኔታዎች የሚመለከት ነው፡፡ ራሴ መርጬ የገባሁበት ትልቅ ቢሮ ነው፡፡ የእስራኤልን ሕዝብ፣ ወገኔን ኢትዮጵያዊው ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሕዝብ ጥቁሮችም ስደተኞችንም በተለያዩ ሁኔታዎች አገለግላለሁ፡፡ ችግር አለ፡፡ መፍትሔም ማምጣትም አለ፡፡ በየአጋጣሚው ወጣቶቻችን ከፖሊስ ጋር የሚጋጩበትን ችግር ለመቀነስ እጥራለሁ፡፡ እስራኤልን ወክዬ ለጥቁር ኅብረተሰብ ወገኖቼ እሆናለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ተመካክረን በመሠራት እዚህ ያሉትን ኢትዮጵያኖች በሙሉ ማንነትና ደኅንነታቸውን መብታቸውን ለማስከበር ችላ አልልም፡፡ ሥልጣን መያዜ ትልቁ ክብሬ ነው፡፡
“የጥቁር አይሁድ” – “የፈረንጅ አይሁድ”
ለቤተ እስራኤሎች አንዱ ፈተና የነበረው የሃይማኖት መሪዎቻቸው ራባዮች በሌሎች ያላቸው ተቀባይነት እምብዛም አልነበረም፡፡ ይህንኑ ሁኔታ ለማስተካከል ለአራት አሠርታት ያህል ትግል ተካሂዷል፡፡ በተለይ ከሁለት አሠርት ወዲህ አቶ ጋዲ ባደረጉት እንቅስቃሴ ስኬት ተመዝግቧል፡፡ አቶ ጋዲን የችግሩ መንስዔ ምንድነው ብለን ጠየቅናቸው እንዲህ መለሱ፡፡
እኛ ቤተ እስራኤሎች በአፍሪካ ስላለን እንደ አሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂም ስላልነበረ ለብቻችን ተነጥለን በመኖራችን ‹‹የፈረንጅ ቤተ እስራኤል የለም›› ብለን እናምን ነበር፡፡ የማስታውሰውን በታሪክም ያነበብኩትን እዚህ ላይ ላንሳልህ፡፡ በተወለድሁበት ስሜን አውራጃ የመጡ ፈረንጆች ‹‹እኛ እስራኤሎች ነን፤ ከኢየሩሳሌም የመጣን ነን›› ብለው የሃይማኖት መሪዎቻችንን ጠየቁ፡፡ መሪዎቻችንም ‹‹እንዴት የእስራኤል ነጭ ይኖራል፣ ነጭ የለም ሁላው ጥቁር ነው፣ ማንነታችሁን ግለጹልን ብለው ተጠራጥረው በውጭ አስቀመጧቸው፡፡ ፀጉራቸውን ላጭተው ሰባት ቀን ጥሬ ቆርጥመው፣ ሽምብራ በልተው ነው ወደ እኛ ያዘለቋቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ለካ ነጮችም አሉ ብለን ማመን ጀመርን አባቶቻችን እያመኑ መጡ፡፡
ፈረንጆቹም ስለእኛ ‹‹የጥቁር አይሁድ የለውም›› በማለት ብዙ ሲጠራጠሩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው ግጭቱ፡፡ እንዲያውም በዚህ ያሉ የታሪክና የሃይማኖት መሪዎች በእስራኤል ካሉት የሃይማኖት ሰዎች ‹‹ዋናው ንፁሁ እስራኤላዊ ማነው ተብሎ ሲመረመር ካሉት ፈረንጆች የእኛ የቤተ እስራኤል አይሁዶች ልክ በቤተ መቅደሱ እንደነበረው ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በሃይማኖትና በአለባበስ ጥያቄ አድርገው አምነውበታል፡፡
የኢትዮ – እስራኤል ግንኙነት
የሁለቱ ሕዝቦች ትስስር መሠረት አለው፡፡ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እያሳደግን ለመምጣት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር የተለያዩ ፕሮግራሞችን እየነደፍን ነው፡፡ የባህልና ትውፊት ትስስርን በተመለከተ ከአምባሳደሩ አቶ ረታ ዓለሙና ከኤምባሲው ሠራተኞቻቸው ጋር በመሆን እናጠናክራለን፡፡ ክርስትና መሠረቱ አይሁድ ነው፡፡ ሌሎቹ ነጥለው ቢያዩትም በእኛ ግን አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት በብሉይ የነበረው ሥርዓት አሁንም ይከበራል፡፡ በእስራኤል አብዛኛው ቤተ እስራኤል ቢኖርም የክርስትና ተከታይ ወገኖች አሉ፡፡ የኢትዮጵያን ባህልና የአማርኛ ቋንቋን ለማስፋፋት የምንቀሳቀስበት አንዱ ዓላማዬ ነው፡፡ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ሲጨርሱ እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ እንደሚማሩት አማርኛም መማር አለባቸው፡፡ ቋንቋ ክብር ነው ልብስ ነው፡፡ ማንነት እስከሚገልጽ ድረስ ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ለማስፋፋት የምጥርበት ወቅት ነው፡፡
‹‹የሕፃን ሽማግሌ››
‹‹ስለሁለት እናቶቼ ልንገራችሁ›› በማለት ወጋቸውን የቀጠሉት አቶ ጋዲ፣ ‹‹የመጀመሪያዋ ፀንሳ የወለደችኝ እናቴ ወ/ሮ የንጉሥነሽ እሸቴ ትባላለች፡፡ ከ17 ወንድምና እህት የመጨረሻው ልጅ ሆኜ፣ በልዩ ፍቅርና እንክብካቤ አሳድገውኛል፡፡ እናቴ ከልጅነቴ ጀምሮ አብዛኛውን አስተዋጽኦ አድርጋልኛለች፡፡ ካደግሁ በኋላ እነሱ እንደነገሩኝ ‹‹ልጄ አንተ መሪ ነው የምትሆን›› ትል የነበረችው እናቴ ናት፡፡ አባቴም እንዲህ ሲሉ ነው የኖሩት፡፡ እኔ አላስታውስም እንጂ እነሱ አስታውሰው የሚነግሩኝ ታሪክ አለ፡፡ አባቴና እናቴ ሊፋቱ ሲል ማስታረቄ፡፡
አባቴ ደባርቅ ሲኖሩ እናቴ ጥበበኛ ስለሆነች ስሜን ሆና ሸክላ ትሠራ ነበር፡፡ ከአንዱ አገር ሸክላ ልትሠራ ልትሄድ ስትል አባቴ ልጆቼን ላይ ነው ብሎ ይመጣል፡፡ እናቴ ልትሄድ ስትነሳ አንድ ነገር ላማክርሽ ነው፣ ቃል ግቢልኝ እላታለሁ፡፡ “አባቴ ይሙት፣ እናቴ ትሙት በዪ” ብዬ ካስማልኳት በኋላ፣ ከዛሬ ጀምሮ ከአባቴ ጋር እንድትሆኚ አልኳት፡፡ ከሽ አለች (እኔ አላስታውስም የሚነግሩኝ እነርሱ ናቸው)፡፡ እኔ ያልኳትን ብላ ተደብቃ ሠርታ አልቅሳ እሺ አለችኝ፡፡ በነጋታው አባቴ ሊሄድ የነበረው ከአባቴ ጋር አደሩ፡፡ ሽማግሌዎን እምቢ ያላቸውን በልጅነቴ እኔ አስታርቄያቸው ወደ እስራኤል አብረን ተጉዘን፣ ከአሥር ዓመት በፊት አባቴ ከዚህ ዓለም እስከ ሚለዩ ድረስ አብረው ኖሩ፡፡ ወላጆቼ ከልጅነቴ ጀምሮ እንደ ትልቅ ያዩኝ ነበር፡፡
ለሁለተኛዪቱ እናቴ ለኢትዮጵያ ያደረግሁላት ነገር አለ፡፡ በፓርላማ ቃለ መሐላ ልገባ ስል የስሜን ፓርክ ሲቃጠል ነበር፡፡ ፓርኩ ሲቃጠል ዝምብለን አላየንም፡፡ ይቺ አገራችንም ናት እሳቱን ማጥፋት አለብን ብለን ተነሳን፡፡ የእሳት አደጋ ቡድን ሄደ፡፡ ፓርኩም እንዲያገግም ደን እንዲለብስ የራሳችን አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡
ኢትዮጵያዊ ስሜት
ኢትዮጵያ ማለት ለእኛ ለቤተ እስራኤሎች በተወሰነ ዘመን አባቶቻችን የነገሡባት፣ ያደጉባት፣ የተዋጉባት፣ የሞቱባት፣ በክፉ ዘመንም የተሰደቡባት፣ የተገደሉባት ይህም ሆኖ አገራችን ስለሆነች የምንወዳት አገር ናት፡፡ በተለያዩ ዘመኖችም ቤተ እስራኤል በኢትዮጵያ ሲኖሩ የኢትዮጵያን ቅርፅ ይዘው የወጡ፣ የኢትዮጵያን ጥበብ የሠሩ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ የጻፉ፣ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያፈሩ ናቸው፡፡
አሁን እንኳን በጎንደር አካባቢ ቢኬድ በኢትዮጵያ ካርታ ላይ አባቶቻችን የመሬቱ ባለቤቶች ስማቸው አለ፡፡ በነገሥታቱ ዘመን የቤተ እስራኤል የአሥራ ሁለቱ ነገድ ስሞች አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ልጆች ዘሮች ስለሆንን ለእኛ ኢትዮጵያ ማለት የምንወዳት አገርና የምናከብራት አገር ናት፡፡ እኔ ለኢትዮጵያ ያለኝ ሐሳብና ፍቅር በጣም የተለየ ነው፡፡ በስምንት ዓመቴ ለቅቄ ብመጣም ግዴታ አማርኛዬን ላሻሽል የቻልሁት ከአማርኛ ፍቅር፣ ከሙዚቃው፣ ከባህላችን፣ ከልብሳችን 3‚000 ዓመት በላይ ካላት ታላቅ አገር ነው፡፡ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዓለም ካሉት አገሮች ነፃነቷን አስከብራ የኖረች፣ የምትኖር አገር ናት፡፡
ያዘጋጁት መጽሐፍ
“ሕይወት እንደገና” የሚል በዕብራይስጥ ቋንቋ ጽፌያለሁ፡፡ የቤተ እስራኤል በሱዳን በኩል ያደረጉትን ጉዞ ችግሮችና ደስታዎችን ይዟል፡፡ ከሦስት ሺሕ ዓመት በኋላ ያገኘናት አገራችንን የሚጠቅሱ ጥቅሶችንም ጽፌያለሁ፡፡