በሶፎንያስ ዳርጌ እና አባዲ ግርማይ
ከዓመታት በፊት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የዕፀዋት ማዳቀል (Plant breeding) የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች መካከል ሳይንሳዊ ሙግት የማድረግ ባህል ነበር። በየዓመቱ የድኅረ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች በሁለት ቡድን ተከፍለው ይሟገታሉ። አንደኛው ቡድን “ልውጥ ሕያዋን (GMOs) ያላቸውን ጠቀሜታ በመደገፍ”፣ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በተቃራኒው በመቃወም ይከራከራሉ፡፡ በሁለቱም ወገን የሚደረጉ ሳይንሳዊ ሙግቶች የሚዳኙት ከተለያዩ የሙያ መስኮች በመጡ የሙግቱ ታዳሚዎችና በመምህሮቻቸው ነበር፡፡ ይህ የግራና ቀኝ ሙግት ከጭፍን መቃወምና ጭፍን መደገፍ በተሻለ መልኩ ከሁለቱም ወገን በሚቀርቡ ሳይንሳዊ መከራከሪያ ነጥቦች ስለ ልውጥ ሕያዋን (ጂኤምኦ) ያለንን ብዥታ እንድናጠራ ያገዘ አጋጣሚ ነበር፡፡

ልውጥ ሕያዋን የበሽታ መከላከል አቅምን በማሳደግ ምርት እንደሚጨምሩ፣ የተሻለ የተመጣጠነ ምግብነት እንዳላቸውና በተለይም ለፋብሪካ ምርት እጥረት እንዳያጋጥም በብዛትና በጥራት ለማምረት ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ይከራከራሉ፡፡ በተቃራኒው ልውጠ ሕያዋንን (ጂኤምኦ) መጠቀም የአፈር ጥቃቅን ሥነ ሕይወታውያንን ይጎዳል፣ ብዝኃ ሕይወትን ያናጋል፣ የገበሬዎችን የዘር ጥገኝነት ያስፋፋል፣ የአለርጂና ካንሰር በሽታን እንደሚያመጣ ወዘተ እያሉ የሚከራከሩት ደግሞ ወደ አገራችን መግባት የለበትም የሚሉት ወገኖች ናቸው፡፡
ዛሬ ላይ የሃረማያው ግራና ቀኝ የልውጥ ሕያዋን ሙግት መንግሥት ደጅ ረግጧል፣ የአገር ፖሊሲ ሁነኛ የአደባባይ ሙግት ሁኗል። ነገር ግን በአብዛኛው በልውጠ ሕያዋን ዙርያ የሚደረጉ ሙግቶች እንደ ሃረማያው ዩኒቨርሲቲ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታና ያለንን ሀብት መሠረት ያደረጉ ሳይንሳዊ ሙግቶች አይደሉም፡፡ እንደውም ከዚህ ከፍ ባለመልኩ የኮርፖሬቶች አፍ ወደ መሆን ያዘነበሉ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. የካቲት 5 ቀን 2020 የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንት የውጭ አገሮች የግብርና አገልግሎት ኢትዮጵያ በልውጠ ሕያዋን ዙርያ ከምትታወቅበትና የፓን አፍሪካ አቋም ተደርጎ ይወሰድ ከነበረው የቀደመ ፅኑ ሐሳቧ በተቃራኒው መቆሟን እንዳስደሰተው ከገለጸ በኋላ፣ በአገራችን ዓብይ የመወያያ ርዕስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለገበያ የሚሆን የጥጥ ምርት እንደፈቀደና ልውጠ ሕያዋን የሆኑ የእንሰት ተክልና በቆሎ የሙከራ ሒደት እንዲደረግ መፍቀዱንም የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንት በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ይህ ዜና ከተሠራጨበት ጊዜ ጀምሮ በጉዳዩ ላይ አሉ የሚባሉ፣ ጉምቱ የአገራችን ምሁራንን ወደ ክርክር ሜዳው የጋበዘና አንዳንዶቹ ክርክሮችም በጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ የታጀቡ ናቸው፡፡
የሚገርመው ነገር ይኼ በይዘቱ የተንጋደደ ሪፖርት በመግቢያው ላይ “የኢትዮጵያ ገበሬዎችና ተመራማሪዎች የምግብ ደኅንነትና የዕፀዋት ጤንነት ችግሮችን ለመፍታት በተለመደው የማሻሻያ ሥርዓት (conventional breeding) ብዙ ሞክረዋል። ነገር ግን ምንም ውጤት ሊያስገኝላቸው ስላልቻለ ፊታቸውን ወደ ዘመናዊው የባዮቴክኖሎጂ አማራጭ እያዞሩ ይገኛሉ” ይላል። ይህ ከእውነት የራቀና ምናልባትም የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንትን ጥልቅ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ታሪክ በአንጻራዊንት አጭር ዕድሜ ያለው ነው ቢባልም ከተጀመረበት ከ1960ዎቹ ወደዚህ ለኢትዮጵያ የግብርና ዕድገት ወሳኝ የሚባል ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ማንም በቀላሉ ሊገነዘበው የሚችል ነው። በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በሌሎች አካላት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተገቢው ቴክኖሎጂ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት የሆኑት በዋናነት ዝቅተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ሥርፀት፣ በጣም ዝቅተኛ የግብዓት አጠቃቀም፣ የመሬት ፖሊሲ ችግሮች፣ ያላደገው የገጠር የመሠረት ልማት፣ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች፣ የብቁ ተመራማሪዎች ፍልሰትና የመሳሰሉት ናቸው።
በሪፖርተር ጋዜጣ የግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕትም መኮንን ተሾመ ቶሌራ “የሳይንቲስቱ ሳይንሳዊ ያልሆነ ሙግት” በሚል ርዕስ ያስነበበን ሐተታ ከብዙዎቹ አንዱ ነው፡፡ ጸሐፊው በሐተታው የልውጠ ሕያዋንን ጥቅም በሚገባ የገለጹ ሲሆን ቴክኖሎጂው አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ጥረዋል፡፡ ጸሐፊው ተወልደ ገብረእግዚአብሔር (ዶ/ር) የልውጥ ሕያዋን በተመለከት “An open letter to the government of Ethiopia” በሚል ለመንግሥት ያቀረቡትን ሐተታ ላነሷቸው መከራከሪያ ነጥቦች የሚያጎላና የሚጎለብት ሳይንሳዊ መረጃ አላቀረቡም በሚል ከሙግት ይልቅ ዘለፋ በሚባል ደረጃ የዶ/ር ተወልደን ሐተታ ወርፈዋል፡፡ “Ethiopia Observer” ይዞት በወጣው የዶ/ር ተወልደ ሐተታ “የልውጥ ሕይወት በባዮ ሴፍቲ እና በአካባቢ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች ማክበር እንደሚገባት” ያብራራል፡፡
ነገር ግን መኮንን ተሾመ ቶሌራ ከዐውዱ ውጭ በሆነ አተረጓጎም ሳይንሳዊ መረጃ ሳያቀርቡ፣ “ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የአካባቢ ጥበቃ ጠበቆች የዘረመል ምሕንድስና ሳይንስን ሚዛናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከማየት ይልቅ፣ የራሳቸውን ፍላጎትና ምኞት ብቻ ማየታችው ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ አገርንም የሚጎዳ ነው፤” በማለት ዶ/ር ተወልደ በመጣጥፋቸው ስለ ልውጠ ሕያዋን መልካምና መጥፎ ጎን እንኳ አጀንዳቸው ባላደረጉበት ጽሑፍ፣ እሳቸውን ለመዝለፍ ረጅም ርቀት መሄዱ ያስተዛዝባል፡፡ በድኩም አመክንዮ የትልቆችን ሐሳብ ለመዘንጠል ወደኋላ የማይሉ ሰዎች ሲያጋጥሙ ይህን የገጣሚ ኑረዲን ዒሳ ግጥም ማስታወስ ያሻል፦
“አልሆን ያለህ ጊዜ፣ ማደግና መግዘፍ
ከታላቆች መሃል አንዱን መርጠህ ዝለፍ፡፡”
አቶ መኮንን ተሾመ “ልክ የኑኩሌር ኃይል በጥንቃቄ ከተያዘ ለኃይል ማመንጫነት፣ ግዙፍ ማሽኖችንና ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስ እንደሚጠቅመው ወይም በተቃራኒው ለጥፋት እንደሚውለው፣ ወይም ደሞ ሌሎች ጠቃሚ ነገሮችን ገና ለገና ጉዳት ያመጣሉ ብለን መተው እንደሌለብን ወሳኝ ነገሮች፣” እንዲሁም “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም!” እንደሚሉት፣ ለምሳሌ ገና ለገና አውሮፕላን ይከሰከሳል ብለን ከመጓዝ እንደማንታቀበው፣ ገና ለገና ሁሉም መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው ብለን ክኒን አንውጥም እንደማንለው፣ ገና ለገና ልንሞት እንችላለን ብለን በሐኪሞች ቀዶ ሕክምና አንደረግም እንደማንለው ወዘተ፤” የሚሉና ሌሎች ድኩማን የሙግት ሐሳቦች በማንሳትና ልውጠ ሕያዋን ወደ ኢትዮጵያ ካልገባ የኋላ ቀርነታችን ማሳያ፣ የኢኮኖሚና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደማንችል ተደርጎ የሞትና የሕይወት ጉዳይ አድርገው ለማቅረብ የደከሙት ድካም ያሳዝናል፡፡ ዶ/ር ተወልደ ለአገራቸው ለሠሩት ሥራ እጅግ ሊመሰገኑ እንጂ ሊወገዙና ሊዘለፉ ባልተገባ ነበር፡፡
ትምህርትና ተግባራዊነቱ
የባዮቴክኖሎጂና የሞሎኪዩላር ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከሳይንስነቱ ባሻገር ለሳይንቲስቶች “በተፈጥሮ ላይ የመጫወት” (artificial genetic manipulation) ዕድል ስለሚሰጥ አድካሚም እንኳ ቢሆን አዝናኝ የሥራ ዘርፍ ነው። የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 7 ቀን 1986 ባወጣው ለየት ያለ ዘገባው፣ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሳንዲያጎ የሚገኝ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን በአብሪ ትል ውስጥ የሚገኝ ዘረመል (gene) ወደ ትምባሆ ተክል በማስተላለፍ የትምባሆው ማሳ በሌሊት እንዲያበራ ማድረጋችውን ያትታል። ይኼ ግኝት በወቅቱ ለተመራማሪ ቡድኑና ለሕዝቡ ሊሰጠው የሚችል አግራሞት መገመት ይቻላል። አሁን የምንገኝበት የሲንቴቲክ ባዮሎጂ ዘመንም ከዚህ የሚልቁ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ግኝቶችን በየጊዜው ያሳየናል። በየአገሮቹ የሚገኙ ጥብቅ የድኅነተ ሕይወት ሕጎችና ክልከላዎች (Biosafety rules and protocols) ባይከለክሏችው በዘርፉ ከጠቃሚ ግኝቶች ባሻገር የሰው ልጅን ደኅንነት የሚፈታተኑ ብዙ ኢሞራላዊና ሕገወጥ ሥራዎች በተሠሩ ነበር።
በኢትዮጵያም የደኅንነተ ሕይወት አዋጁን /የሕግ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 655/2009/ በልውጥ ሕያዋን ተመራማሪዎች ዘንድ የተማሩት ትምህርት በተግባር ላይ ለማዋል እንቅፋት እንደሆነባቸው መስማት የተለመደ ነው፡፡ የቀለም ትምህርት ተግባር ላይ ማዋል (professional exercise) አብዛኛው ምሁር የሚፈልገው ቢሆንም አንዳንዴ የተማሩት ትምህርት ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድና ትልቁን የአገርን ጥቅም አሳልፎ እንደማይሰጥ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
የምግብ ዋስትና አለማረጋገጥ እንደ ምክንያት
ጠግቦ ለማያድር ሕዝብ ምግብ ማማረጥ ምኑ ነው? እና የምግብ ዋስትና ያላረጋገጠች አገር የምግብ ሉዓላዊነት እንደሌላትና ምዕራባውያን የኛ ጠግቦ አለማደር ያሳሰባቸው ተደርጎ የሚቀርበው ሙግት ውኃ አያነሳም፡፡
የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ የምግብ ዋስትና አለማረጋገጥ በዚህም ለተደጋጋሚ ድርቅ ተጋላጭ መሆን፣ የኢኮኖሚ አለማደግ፣ ግብርናው ኢንዱስትሪውን በበቂ ሁኔታ አለመደገፍ እንደ ምክንያት በመጥቀስ የልውጥ ሥነ ሕይወታዊ ዘር ወደ ኢትዮጵያ መግባት አለበት በማለት ይሞግታሉ፡፡ በዓለም በተለይም ባደጉት አገሮች ‘ውጤታማነቱ’ ስለተረጋገጠ ባላደጉ አገሮች ያንን ይደግመዋል ማለት እንዳልሆነ አፍሪካን መሠረት በማድረግ የተሠሩ የምርምር ውጤቶች ያመላክታሉ፡፡
ያላደጉ አገሮች አርሶ አደሮች ማለት ምን ማለት ነው? የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ባለትንሽ መሬት ይዞታ ገበሬዎች እንዴት ያሉት ናቸው? የሚለውን ዳቬንድራ የተባለ ምሁር የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅትን ጠቅሶ እንደጻፈው፣ “ያላቸውን እንዳያጡ በሥጋት ውስጥ የሚኖሩ፣ ዝቅተኛ ኑሮና ገቢ ያላቸውና ያልተማሩትን ያጠቃልላል” ይላል፡፡ በዚህ ብያኔ መሠረት የኛው አገር ገበሬዎችም ይጠቃለላሉ፡፡
ልውጥ ሕያዋንና ድሃ ገበሬዎች ምንና ምን ናቸው?
አሂቶና ባልደረቦቹ “Implications of GM crops in subsistence-based agricultural systems in Africa” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደ መፍትሔ የሚቀርቡ የልውጥ ሕያዋን ቴክኖሎጂዎች የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ በመሆናቸው ውጤታማነታቸው እምብዛም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም ማለት ደካማ የግብርና መዋቅር፣ የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር፣ የገበሬው ብዙ ዓይነት ዝርያዎችን ለማብቀል መፈለግ፣ የአካባቢንና ኅብረተሰቡን ሊጎዳ እንደሚችል ያብራራሉ፡፡ ለምግብነትና ለምርት የሚጠቀመው ዘር ብዙም ልዩነት በሌለበት አፍሪካ ይህን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ከመታሰቡ በፊት ሊሟሉ የሚገባቸው ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሮበርት ፊንገር (Robert Finger) እና ባልደረቦቹ “A Meta Analysis on Farm-Level Costs and Benefits of GM Crops” በሚለው ጥናታዊ ዳሰሳቸው፣ ትርጉም ባለው መልኩ ልውጥ ህያው ጥጥ ከነባሩ የጥጥ ዝርያ የተሻለ ምርት የተገኘው በህንድ ብቻ ነው፡፡ ጥናቱ በአሜሪካ፣ አውስትራሊያና ቻይና የተሻለ ምርት እንዳላስገኘ አመላክቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገበያ ላይ ያለው የልውጥ ሕያዋን ምርት ከመጨመር ሌላ በተለይም ዝቅተኛ የአፈር ለምነትን፣ ጨዋማነትን በሚፈታ መልኩ እንዳልተሠሩ ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም ልውጥ ሕይወት መጠቀም በራሱ ድህነትን ወይም የምግብ እጥረትን ይቀርፋል ማለት እንዳልሆነ ያሰምሩበታል፡፡
እውቁ የአገራችን ሳይንቲስት ዶ/ር መላኩ ወረደ ከቴክ ቶክ አዘጋጁ ሰለሞን ጋር በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በነበራቸው ቆይታ፣ ልውጥ ህያው ጥጥ /Bt-cotton/ የትሮይ ፈረስ ይሉታል፡፡ “ከናሽናል ኮርፖሬሽኖች ጋር ብንዋዋል ለአገራችን የምግብ ሰንሰለት ትልቅ አደጋ ነው የምንደቅነው፡፡ ኮርፖሬቶቹ ጥጥን እንደ መግቢያ ተጠቅመው ወደ ሌሎች ሰብሎች ይቀጥላሉ፡፡ አሁንም ሙከራ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ ይህም በበቂ ጥናትና ጥንቃቄ ስለማይደረግ የዘር መበከል ሊያጋጥመን ይችላል፤” በማለት ያላቸውን ሥጋት ይገልጹና “ቴክኖሎጂ እንፈልጋለን፣ የተሻሉ ቴክኒኮችም ያስፈልጉናል፣ እኔ ከቴክኖሎጂ በተቃራኒው የቆምኩ አይደለሁም፡፡ ብዙ ድርቅን ለመቋቋም የሚረዱ የግብርና ቴክኒኮችና ሰብሎች አሉ፣ እነሱን መጠቀሙ ይበጃል፤” በማለት ይገልጻሉ፡፡
ልውጥ ሕያዋን መጠቀም ውጤታማ ሊያደርግ የሚችለው ተመሳሳይ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድር ባላቸው እንደ ካናዳና አሜሪካ ባሉት አገሮች እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በተበጣጠሰ መሬት ላላት፣ በአንድ ኪሎሜትር እንኳ የተለያየ የአፈር ዓይነትና ብዙ የብዝኃ ሕይወት ሀብት ባላት አገራችን መሞከሩ ጉዳቱ የበዛ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በሕዝብ ብዛት መጨመር ምክንያት ለኢኮኖሚ መዳከምና የምግብ ዋስትና አለማረጋገጥ መዳረጋችን በዘርፉ ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀን አመላካች እንጂ የነዚህ ሁሉ መፍትሔ ልውጠ ሕያዋን መጠቀም አድርጎ ማሰቡ አያስኬድም፡፡
ኢትዮጵያ፣ ድሃ ገበሬና ልውጠ ሕያዋን
በዚህ ዘመን፣ አንዳንዱ የተማረው ትምህርት ተግባራዊ እንዳያደርግ በመከልከሉ፣ ገሚሱም የኮርፖሬቶች ረጅም አፍ በመሆኑ፣ ሌላውም እጅግ ወግ አጥባቂና አዲስ አስተሳሰብ ጠል በመሆን፣ አንዳንዱም ከአገሩ ሁናቴ ጋር የማይሄድ በመሆኑ ወገን ለይቶ ይሟገታል፡፡ ምሁሮቻችን ከዚህ ምን ያህል ነፃ ናቸው?
ተሾመ ሁንዳሞ፣ “ኢትዮጵያ የግብርና ችግሮችን ለመቅረፍ የልውጥ ሕያዋን እንደምትቀበል የአሜሪካ የግብርና ዲፓርትመንት ቢገልጽም በተግባር ግን ልውጥ ሕያዋን በብዙ የአፍሪካ አገሮች ጨምሮ በአውሮፓ ኅብረት አገሮችና በሌሎች ተቀባይነት እንደሌለው ግሁድ ነው፤” ይላሉ፡፡ ቀጥለውም “ለምን አፍሪካ ውስጥ? ለምን በዚህ ጊዜስ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ተፈለገ? የሚሉትን ጥያቄዎች ማጤን ያስፈልጋል” ሲሉ ያክላሉ፡፡ ለውሳኔዎቹም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችና ባለድርሻ አካላት በተለይም አርሶ አደሩ የምክክሩ አካል ሊሆን ይገባል፡፡
ዶ/ር መላኩ፣ “ማንኛውም ከግብርና ግብዓት ማሻሻልና መቀየር ጋር የሚያያዝ ነገር ለዘመናት ጠብቆ ያቆየልንን አርሶ አደሩን ሳያማክሩና ፍላጎቱን ሳይጠይቁ ከላይ ወደ ታች ለመጫን የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች አደጋቸው ብዙ ነው፡፡ በመጀመርያ ያሉንን የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን ጠንቅቀን በማወቅና እነሱን በተሻለ መልኩ መጠቀሙ ይቀድማል፤” ይላሉ፡፡
በገበሬው አመለካከት ምርት ብቻውን ዘርን ለመምረጥ መሠረታዊ ምክንያት አይደለም፡፡ በወቅቶች ሰብሎችን ስለማቀያየር፣ መልክዓ ምድር፣ ጣዕም፣ የተለየ ምርት ለተለየ ባህላዊና ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ለማዋልና ሌሎችም ምክንያቶች መሠረት አድርገው ሰብሎችን ይመርጣሉ፡፡ ለአርሶ አደሮች ትልቁ መመዘኛ ቀጣይነት (sustainability) ነው፡፡
ብዙዎች የገበሬውን የዘር ባለቤትነት ተላልፎ እንዳይሰጥና የምዕራባውያን ተቋማት ጥገኛ እንዳይሆን እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡ ባለትንሽ መሬት ይዞታው አርሶ አደር ይህን ቴክኖሎጂ ቢጠቀም ምን ይጎዳል፣ ምንስ ይጠቀማል ብሎ ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡
ሁሴን አዛዲና ባልደረቦቹ እ.ኤ.አ. በ2015 “Genetically modified crops and small-scale farmers: main opportunities and challenges” በሚለውና ትንሽ መሬት ላላቸው ገበሬዎች ልውጥ ሕያዋን መጠቀም ያለው ጥቅምና ተጓዳኝ ጉዳት በሚያብራሩበት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ በተለይም ገበሬዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ዘሩን መጠቀም እንዳይችሉ የሚያግድ መሆኑ፣ በዋጋም ውድ መሆኑና ዘር መዋዋስም ሆነ መገበያየትን አጥብቆ መከልከሉ ለእንደ አፍሪካ ላሉ አህጉራት ገበሬዎች ሌላ ራስ ምታት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በሰብል ደኅንነት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪው ተሾመ ሁንዱማ ለኢትዮጵያን ኢንሳይት /Ethiopian Insight/ በጻፈው መጣጥፍ ላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ ሊባል የሚችል የጅን ባንክ ባለቤት እንደሆነች ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጅን ባንክ እስካሁን 86,599 የዘር ናሙናዎች ከ100 በላይ የሰብል ዝርያዎች /አብዛኛዎቹ የምግብ ሰብሎች ናቸው/ ከአገሪቱ ለመሰብሰብ እንደቻለ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ከገበሬው ጎን እንዲቆምና የዘር ባለቤትነቱን ተላልፎ እንዳይሰጥ ያሳስባሉ፡፡
በታዳጊ አገሮች ልውጥ ሕያዋን ከማስተናገዳቸው በፊት በተለይም በዘርፉ የተደራጀ የምርምርና ቁጥጥር አቅም እንዲኖራቸው ይመከራል፡፡ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ባልተዘረጋበት ሁናቴ ገፋፍቶ ለማስገባት መሞከር ራሱ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች እንድታከብርና ምሁራዊ ሙግቱ ከዘለፋ በዘለለ ሳይንሳዊ ማስረጃ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታና ያለን ሀብት ያገናዘበ መሆን ይገባዋል፡፡ የውሳኔ ሒደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያሰፈነና ባለድርሻ አካላትን ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹ አቶ ሶፎንያስ ዳርጌ በአፈር ሳይንስ፣ አቶ አባዲ ግርማይ በዕፀዋት ማዳቀል የማስተር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ያላቸውና ተመራማሪዎች መሆናቸውን፣ መጣጥፉም የእነሱን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] እና [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡