አቶ ጃዋር መሀመድ “በማላውቀው ሀኪም መነካት አልፈልግም” በማለቱ በግል ሀኪም እንዲታከም ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጠ
_ የዓቃቤ ሕግ ምስክርሮችን መሰማት ጀመረ
አቶ ጃዋር መሀመድ ከአራት ቀን በፊት ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓም እንደታመመ ለፍርድ ቤት በማስረዳት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ሳይሰሙ ለዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓም በተቀጠረው መሠረት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ።
ምስክሮች ከመሰማታቸው በፊት ፍርድ ቤቱ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓም የሰጣቸው ትዕዛዞች መፈጸም አለመፈጸማቸውን አረጋግጧል። በዚህም መሰረት አቶ ጃዋር መንግስት ሳይሆን በመንግስት ውስጥ ያሉ ሰዎች ስጋት እንደሆኑበትና ለህይወቱ ስለሚፈራ በግሉ ሀኪም ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን ቢስት እንኳን በመንግስት ሀኪም መመርመር እንደማይፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በጣም መታመሙን፣ምግብ ሲመገብ እንደሚያስመልሰውና አሁን ላይ ደግሞ እያስቀመጠው መሆኑን አስረድቷል።
ዓቃቤ ህግ በሰጠው አስተያየት ለአቶ ጃዋር ሕክምና እንዲያገኙ ተጠይቀው በግል ሀኪሜ ከልሆነ አልታከምም እንዳሉ ገልጿል።አቅርቦቱ እያለ አልፈልግም እያሉ ወደሌላ ሀኪም ቤት መውሰድ ስልጣንን አላግባብ መጠቀም መሆኑን ጠቁሞ በህግ ፊት ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለውን ሕገመንግስታዊ ድንጋጌም የሚጥስ መሆኑን አክሏል።ወደ ግል ሀኪም ሪፈር ሊደረጉ የሚችሉት ከመንግስት ሕክምና በላይ የሆነ ህክምና ሲያስፈልግ ብቻ መሆኑንም ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን በሕገመንግስቱ አንቀጽ 21 ድንጋጌ መሠረት አቶ ጃዋር በግል ሀኪም እንዲታዪ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።