የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር- የዞን አምስት (አኖካ ዞን 5) ፕሬዚዳንት ሆነው በከፍተኛ ድምፅ ተመረጡ፡፡
አኖካ ዞን-5 በክፍለ አኅጉሩ የሚገኙ አሥራ አንድ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎችን ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ዑጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ያቀፈ ነው፡፡
ዞናዊው አኖካ ቅዳሜ ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢንቴቤ፣ ዑጋንዳ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው፣ ዶ/ር አሸብር ተፎካካሪያቸውን የግብፅን ተወካይ ኤሌሪያን ሸሪፍን ያሸነፉት በ7ለ3 የድምፅ ልዩነት መሆኑን ዴይሊ ሞኒተር ከስፍራው ዘግቧል፡፡
ሱዳናዊው ሁሳም ሆጃሊ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ደቡብ ሱዳናዊው ቶንግ ዴራን ዓቃቤ ነዋይ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ከተመረጡት መካከል አቶ ሉል ፍሥሓዬ (ኤርትራ) ይገኙበታል፡፡ የኬንያው ፍራንሲስ ሙቱኩ ዋና ፀሐፊ ሆነው ያለምንም ተፎካካሪ መመረጣቸውን ዘገባው አክሏል፡፡
በዞኑ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) አባላት ያለ ውድድር በቀጥታ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ፣ ከነዚሁም መካከል ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ ብርሃነ (ኢትዮጵያ) እና ተሰናባቹ ዑጋንዳዊው ፍሬድሪክ ብሊክ ይገኙበታል፡፡
አዲሱ ፕሬዚዳንት አሸብር ለአራት ዓመታት አኖካን ከመሩት ዑጋንዳዊው ብሊክ መንበሩን በተረከቡበት ወቅት ባሰሙት ዲስኩር፣ ‹‹እንደ ዞን ለስኬት አብረን መሥራት አለብን፡፡ በግልጽነት ለማስተዳደር ቃል እንገባለን፤›› ካሉ በኋላ ለዚህም ካለፈው አመራር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመሥራት ቃል መግባታቸው ዘገባው ጠቄመዋል፡፡
ተሰናባቹ የአኖካ ዞን አምስት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ቢልክ በዘመናቸው በትጋት ማገልገላቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ለአባላት ንቁ ተሳትፎ፣ በዞኑ የወጣት ጨዋታዎችን በማካሄድ፣ ከዞኑ ወደ ኦሊምፒክ የተጨመሩ የአትሌቶች ብዛትና ሌሎች በርካታ በመሆናቸው በሥራዬ ዘመን ብዙ ነገሮችን አሳክተናል፡፡ ለተሻለ ሥራ ሕገ ደንቡን መገምገም አለብን፤›› ተናግረዋል፡፡
‹‹ሁሉንም አሸናፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ በአኖካ ዞን አምስት ውስጥ ለስፖርቶች ልማት ስኬት አመራሮቹ አንድ ሆነው እንዲቀጥሉ አደራ እላለሁ፤›› ያሉት የአኖካ ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ቢራፍ፣ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ እሴቶችን ለማሳካት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያና አኖካ
አምሳ አራት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ)፣ ከአራት አሠርታት በፊት በናይጄሪያ ሲቋቋም ለምሥረታው ዓይነተኛ ሚና ከነበራቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ኢትዮጵያዊው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው፡፡ ነፍስ ኄር ይድነቃቸው በወቅቱ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖችን የሚያስተሳስረው የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር (ዩካሳ) መሥራችና ፕሬዚዳንት ስለነበሩ አኖካ ተመሥርቶ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በርሱ ሥር እንዲከናወንም አልመው ነበር፡፡
በሰኔ 1973ቱ የአኖካ መሥራች ጉባዔ የቶጎው አናኒ ማቲያ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ፕሬዚዳንትና የስፖርት ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ጸጋው አየለ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ አኖካ ከአራት ዓመት በኋላ የመጀመርያ ጉባዔውን በአዲስ አበባ አፍሪካ አዳራሽ ሲያካሂድ፣ አቶ ጸጋው በስፖርትና በኦሊምፒክ መድረኮች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ፣ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይሁንታ አግኝተው በወቅቱ ፕሬዚዳንት ጁዋን ኦቶንዮ ሳማራንሽ አማካይነት፣ ርእሰ ብሔር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በተገኙበት የኦሊምፒክ ኦርደር ሜዳይ (the silver medal of the Olympic Order) ተሸልመዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ከመሸለማቸው በተጨማሪ የአፍሪካ ስፖርት ምክር ቤት የዕድሜ ልክ አባል ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል፡፡
ከአቶ ጸጋው በመቀጠል የአኖካ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ በ2001 ዓ.ም. የገቡት ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ ናቸው፡፡ እሳቸው አኅጉራዊውንም ማኅበር አልፈው፣ በዓለም ደረጃ የተመሠረተውና የኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ አሻራ ያለበት የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖክ)፣ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አባል ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡