ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት ሰማንያኛ ዓመት ረቡዕ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. አክብራለች፡፡ በተለይ በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ በአራት ኪሎው የሚያዝያ 27 አደባባይ፣ የጥንት አርበኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከድል ሐውልት ሥር ጉንጉን አበባ አስቀምጠዋል፡፡
በሥነ በዓሉ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች አገር መባሉ ትልቅ ኩራት ነው፤›› በማለት ዲስኩር ያሰሙት ምክትል ከንቲባዋ፣ ጀግኖች አርበኞች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ሆስፒታሎች በነፃ እንዲታከሙ መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡
ታሪካዊው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም.፣ ፋሺስት ጣሊያን በመስከረም 1928 ዓ.ም. በወልወል በኩል የጀመረችው ወረራ አጠናክራ ለአምስት ዓመታት በወረራ ከያዘችባቸው ግዛቶች በኢትዮጵያውያን ተጋድሎና እርመኛነት በድል የተጠናቀቀበት መሆኑ ነበር፡፡
የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967)፣ በስደትና በዲፕሎማሲያዊ ትግል ከቆዩበት የእንግሊዟ ባዝ ከተማ፣ በሱዳን በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ ላይ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበለቡበት ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላም ከአርበኞች ጋር የዘለቁበትና በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 አዲስ አበባ የደረሱበት ነበር፡፡

የታሪክ ጸሐፊው አቶ ዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚባለው መጽሐፋቸው ስለ ታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 እንዲህ ጽፈዋል፡፡
‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡››
የፋሺስቶች ወረራና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያን መያዛቸው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓ ውስጥ ነው ከሚለው አተያይ በተቃራኒው፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በተፈጸመው ወረራ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩን የታሪክ ምሁራኑ ንጉሤ አየለ (ፕሮፌሰር)፣ አቶ ጥላሁን ጣሰው፣ ዓለሜ እሸቴ (ዶ/ር)፣ ሪቻርድ ፓንክረስት (ፕሮፌሰር) ሞግተዋል፡፡
ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስታዊ መንግሥቷ አማካይነት በአምስቱ ዘመን የሠራችው ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወረራውን በፈጸመች ባመቱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከፈጸመችው ግፍ አንስቶ በሁሉም አካባቢ ብዙ አጥፍታለች፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመርያው የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዘ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡
የታሪክ ባለሙያው አቶ ጥላሁን ጣሰው Trying Times (ትራዪንግ ታይምስ) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደጻፉት፣ ፋሺስት ጣሊያን በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን የወረረችው፣ በቅኝ በያዘቻቸው በሰሜን በኤርትራ በኩልና በደቡብ ምሥራቅ በኢጣሊያን ሶማሊላንድ በኩል በ400 ሺሕ ወታደሮች፣ በ300 የጦር አውሮፕላኖች፣ በ30 ሺሕ ተሽከርካሪዎችና በ400 ታንኮች አማካይነት ነበር፡፡ ሙሶሎኒ በወቅቱ የደረሰበትን ሽንፈት ለመቋቋምና ለመቀልበስ የወሰደው እርምጃ ሠራዊቱ በመርዝ ጋዝ እንዲጠቀም ማዘዙ ነው፡፡ የታኅሣሥ 18 ቀን 1928 ዓ.ም. የሙሶሎኒ ትዕዛዝ በተምቤንና በሐሸንጌ ሐይቅ ለሺዎቹ እልቂት ሰበብ ሆኗል፡፡
‹‹በተምቤን ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ባልሆኑ መሣርያዎች ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድል በማድረጉ ፋሺስት የኬሚካል ጥቃቱን ፈጸመ፡፡ በዚያን ጊዜ ያለቁት 700 ሺሕ የሚደርሱ ናቸው፡፡››
ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት በታተመ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታሪክ ድርሳን ላይ እንደተመለከተው፣ በነገሥታቱ መሪነት ኢትዮጵያን የድል አክሊል እንደተቀዳጀች እንድትኖር ያደረጓት ሕይወታቸውን ስለሠዉላትና የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ አድርገው ስለገነቧት ነው፡፡
ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት በሚል ርዕስ በ1956 ዓ.ም. የታተመው መጽሐፍ የታሪክ ሥፍራዎችና ሜዳዎች፣ የነፃነት ቀኖችና ወሮች ከነዘመናቸው የማይረሱ ናቸው ይላል፡፡ ለምሳሌ ዓድዋና የካቲት 23 ቀን በመቼውም ዘመን በማናቸውም ወርና ቀን ቢሆን ሲታወሱ ትዝ የሚለው፣ በ1888 ዓ.ም. ከጣሊያኖች ጋር ተደርጎ በነበረው ጦርነት የተገኘው ድልና በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ጮራውን የፈነጠቀው የኢትዮጵያ የመታወቅ ዝና ነው፡፡ ድሉም ሲታሰብ አብረው ከሚታሰቡት ከንጉሠ ነገሥቱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጀምሮ ከሠራዊት እስከ መኳንንት የነበሩት የጦር ጀግኖች ናቸው፡፡
‹‹ለአፄ ምኒልክና ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ካሏቸው የድል ቀኖች ዋናዎቹ የካቲት 23 ቀን (1888 ዓ.ም.) እና ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ናቸው፡፡ ከዚህም አስቀድሞ ለነበሩት ለአፄ ዮሐንስ የድል ቀኖችና ሜዳዎች ነበሯቸው፤ እነ ጉንደት፣ ጉራዕ፣ ሰሐጢና ዶግዓሊ የየራሳቸው የድል ቀኖች አሏቸው፡፡
ከስምንት አሠርታት በፊት የተገኘው የሚያዝያ 27ቱ ድል ለመላው ለአፍሪካ ነፃ አወጣጥ መንገድ ጠራጊ መሆኑንም ያመሠጥራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በሰጠችው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከቅኝ ግዛቶቿ የአፍሪካ አገሮች የተመለሱት አፍሪካውያን ወታደሮች ኅሊና ውስጥ ‹‹እኛም ነፃ መውጣት አለብን!›› የሚለው መነሳሳት የታየው በሚያዝያው ድልና ስኬት መሆኑም ተመልክቷል፡፡
እንደ ታሪካዊው ድርሳን አዘጋገብ፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም. ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በፋሺስት ጣሊያን የተያዘችበት) እስከ 1933 ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በድል የተያዘችበት) ድረስ የጠላት ኰቴ በመስኮቿ ላይ ቢዘዋወርም ገዢነቱን አላወቀችለትም፡፡ ጫካው ሁሉ የጃርት ወስፌ ስለሆነበትና ሜዳውም ቢሆን አቃቅማ ብቻ ሆኖ ስላስቸገረው ምን ያህል ጭንቀት እንዳደረበት አምስት ዓመት ያልሞላው የሥቃዩ ዘመን ምስክር ነው፡፡››

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1934 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የድሉ በዓል ይከበር የነበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሲሆን፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ በዓሉን ወደ ‹‹መጋቢት 28›› ለውጦት ከወደቀም በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣ በአምስተኛ ዓመቱ በነባር አርበኞቹና በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ በታሪክ ምሁራንም አረጋጋጭነት በዓሉ በ1988 ዓ.ም. ወደ መሠረታዊ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን ተመልሶ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡